የአፈር ማዳበሪያ በማጓጓዝ ሂደት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት  የምስጋና እና የእውቅና መርኃ ግብር ተካሄደ

መስከረም 7/2015 (ዋልታ) የግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ  ባህርና ትራንስፖርት ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር በ2014/15 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ በማጓጓዝ ሂደት ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላት የምስጋና እና የእውቅና መርኃ ግብር አካሄደ፡፡

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት  አነስተኛ  ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት እንዲያገኙ እንዲሁም ኑሯቸዉንና የማምረት  ባህላቸዉን እንዲያሻሽሉ በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ  ሰፊ ስራ መሰራቱን  የግብርና  ሚኒስቴሩ ዑመር ሁሴን ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ  የግብናዉ ዘርፍ  በተሻሻለ  ሁኔታ ጥሩ ምርት እንዲገኝ የማዳበሪያ  አቅርቦት  ጉልህ አስተዋጽኦ  እያበረከተ እንደሚገኝ  የገለጹት  ሚኒስትሩ በየዓመቱ  በአማካይ  የገበሬዎች የማዳበሪያ አጠቃቀም 20 በመቶ  እያደገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በዓለም  አቀፍ  ደረጃ የተከሰተው  የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት  የፈጠረው  የማዳበሪያ  የዋጋ  ግሽበት እንዲሁም በሀገሪቱ  በአሸባሪዉ የትህነግ ቡድን የተከፈተው  ጦርነት እና የዉጭ  ምንዛሬ አቅርቦት  ችግር በሚፈለገው  ልክ የማዳበሪያ  አቅርቦት  ጥቅም ላይ እንዳይዉል እክል መፍጠሩንም አብራርተዋል፡፡

የማዳበሪያ  አቅርቦት  ከዉጭ  ወደ ሀገር ዉስጥ በባህር  እና በየብስ በማስገባት በኩል  የኢትዮጵያ ባህርና ትራንስፖርት ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ጉልህ ሚና መጫወቱ  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ  ብሄራዊ ባንክ፣  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የክልል ግብርና ቢሮዎች፣ ማሪታይም አገልግሎት የምስጋና እና የእውቅና  ሽልማት ከተበረከተላቸዉ ዉስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት