የአፋር የወጣቶች ምክር ቤት ተቋቋመ

ሚያዝያ 5/2016 (አዲስ ዋልታ) የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር የአፋር የወጣቶች ምክር ቤትን አቋቋሙ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በአፋር ክልል ደረጃ ማቋቋም ወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ዓላማ እንዳለው በመድረኩ ተገልጿል።

ምክር ቤቱ ወጣቶች በመደራጀት መብትና ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን እንዲያረጋግጡና በአገር ግንባታ ሂደት ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ያስችላል ተብሏል።

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ የሺወርቅ አያኔ ወጣቶች ከሌላው ማህበረሰብ የተሻለ ለሀገር ልማትና ለፍትህ፣ ለእኩልነት የተሻለ አበርክቶና አቅም አላቸው ብለዋል።

በመሆኑም ወጣቶች በአገሪቱ ልማትና እድገት ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ በሁሉም ክልሎች የወጣቶች ምክር ቤት መመስረት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

የወጣቶች ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በጅግጅጋ፣ በሀረር፣ በድሬዳዋና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተመሰረተ ሲሆን የሰመራው 5ኛው መሆኑን ተጠቁሟል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የፌደራል እና የክልል የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የተቋቋመው የአፋር ክልል ወጣቶች ምክር ቤት አባላትና ስራ አስፈፃሚዎች ቃለ መሀላ ፈፅመዋል።

አዲስዓለም ግደይና ቅዱስ በለጠ (ከሠመራ)