የአፍሪካ ሀገራት የኮቪድ-19 ክትባት እየተረከቡ ነው

የካቲት 24/2013 (ዋልታ) – በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የመጀመርያ ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ኮቫክስ በተሰኘው ዓለም አቀፍ ጥምረት አማካኝነት እየተረከቡ ነው፡፡

ኬንያ በትላንትናው እለት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን መጠን ያለው ክትባት የተረከበች ሲሆን፣ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሶስተኛዋ የኮቫክስ ክትባት ተጠቃሚ ሆናለች፡፡

በመጀመርያ ዙር የክትባት ዘመቻ 5 መቶ ሺህ ዜጎቿን ለመከተብ ያቀደችው ኬንያ የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራን፣ የፖሊስ መኮንኖች እና አዛውንቶች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ተጠቁሟል፡፡

በዴሞክራቲክ ኮንጎ በመጀመሪያው ዙር 1 ነጥብ 7 ሚሊየን አስትራዘኒካ ክትባት በጤና ሚኒስትሯ ኢቴኒ ሎንጎንዶ በኩል ተረክባለች።

ሀገሪቷ እስከ መጪው ግንቦት ወር 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ክትባት ለመረከብ ማቀዷ ነው የተገለጸው።

በሌላ በኩል አንጎላ 624 ሺህ እንዲሁም ጋምቢያ በትላንትናው እለት 36 ሺህ መጠን ያለው ክትባት ተረክበዋል።

የኮቫክስ ክትባት ዕቅድ በአለም ጤና ድርጅት አማካኝነት የሚተገበር ስትራቴጂ ሲሆን፣ በሀገራት የኮቪድ-19 ክትባትን በፍትሃዊነት ለማዳረስ ያለመ መሆኑን የቢቢሲ አፍሪካ ዘገባ አመላክቷል።

ኮቫክስ የተሰኘው ጥምረት ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለ190 ሀገራት ከ2 ቢሊየን በላይ ክትባት ለማሰራጨት አቅዶ እየሰራ ነው፡፡