የአፍሪካ ቀን ለምን ይከበራል?

በነስረዲን ኑሩ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ቀን አፍሪካዊያን ከውጭ ሃገራት ጣልቃ ገብነት እና ተጽእኖ እራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ያደረጉትን ተጋድሎ ለማሰብ በየአመቱ የፈረንጆቹ ግንቦት 25 ቀን ይከበራል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአውፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1963 በአዲስ አበባ ውስጥ መመስረቱን ተከትሎ ቀኑ መከበር መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መጠሪያ በፈረንጆቹ 2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን በተደረገ ጉባዔ ወደ አፍሪካ ሕብረት መቀየሩ ይታወሳል፡፡

የመጀመሪያው ነጻ የአፍሪካ ሀገራት ጉባኤ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 15 ቀን 1958 ዓ.ም በጋና ዋና ከተማ አክራ የተካሄደ ሲሆን በጉባኤው ተሳተፉት ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ጋና፣ ላይቤሪያ፣ ሊቢያ፣ ሞሮኮ፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ እና ካሜሩን ናቸው፡፡

በእርግጥ ከዚያ ቀደም ብሎ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ በተለያዩ የዓለም ሀገራት አፍሪካን ከቅኝ ገዚዎች ብዝበዛ ለማላቅ ያለሙ ንቅናቄዎች የነበሩ ሲሆን ስለ አፍሪካ ድምጽ የሚሆን ጉባኤ በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ ግን ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡

ይህን ጉባኤ ተከትሎ በአፍሪካ አህጉር የነጻነት እንቅስቃሴ የተፋፋመ ሲሆን አፍሪካ ከውጭ ሃገራት ጣልቃ ገብነት እና ተጽእኖ ነጻ እንድትሆን የሚጠይቁ ድምጾች እና ተቃውሞዎች  ከፍ ብለው መሰማት ጀምረዋል፡፡

በ1958 በጋና የተካሄደው ጉባኤን ተከትሎ የተጀመረው ጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ ተጠናክሮ በመቀጠሉ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከተመሰረተበት የፈረንጆቹ 1963 ድረስ ባሉት አምስት አመታት ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ የአፍሪካ አገራት ራሳቸውን ከአውሮፓዊያኑ ቅኝ ገዥዎች ነጻ ማውጣት ችለዋል፡፡

ዛሬ የሚከበረው የአፍሪካ ቀን የአፍሪካ ቀን ከመባሉ በፊት የአፍሪካ የነጻነት ቀን እና አፍካሪን ነጻ የማውጣት ቀን በሚሉ ስያሜዎች ይከበር ነበር፡፡

የአፍሪካ ሕብረትን በመመስረት ሂደቱ የመጀመሪያ የሆነችውና ለሌሎች አፍሪካዊያን ነጻነት የታገለችው ኢትዮጵያ ዛሬም ለአህጉራዊ ውህደቱ ያላትን ቁርጠኝነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በኩል ዳግም አረጋግጣለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የሚከበረውን የአፍሪካ ቀን ምክንያት በማድረግ በቲውተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክታቸው “አያቶቻችን የነበራቸውን ሰላማዊ፣ የተሳሰረችና የበለፀገች አፍሪካን እውን የማድረግ ራዕይን ለማሳካት ቁርጠኛ ነን” ብለዋል።