ባንኩ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አደረገ

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ባንኩ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ምክንያት በግብርናው ዘርፍ የተያዘው ሀገራዊ እቅድ እንዳይስተጓጉል ትልቅ ሥራ ሰርቷል ብለዋል።

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ዓለምን የፈተነ የዋጋ ንረት ማስከተሉን ጠቅሰው ከፍተኛ የማዳበሪያ አምራች የሆኑት የሁለቱ ሀገራት ግጭት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋና አቅርቦት ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሌሎች የአፈር ማዳበሪያ አምራች ሀገራትም በጦርነቱ ምክንያት ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ረገድ ችግር እንደገጠማቸውም ገልጸዋል።

በዚህም ከጦርነቱ በፊት 700 ዶላር ይሸጥ የነበረው የአንድ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጦርነቱ እንደተጀመረ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ያለው የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እስከ አራት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱንም ነው የጠቀሱት።

ባንኩ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ከሚያደርግባቸው ዘርፎች አንዱ ግብርና መሆኑን ጠቅሰው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ትልቅ ድርሻ እንደሚይዝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ከውጭ የተገዛው ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ሂደቱ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።