የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ኮሚቴ ተዋቀረ

ሰኔ 16/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የፈረመችበት እና በድርድር ሂደቱ እየተሳተፈችበት ያለው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ብሔራዊ የትግበራ ኮሚቴ ተዋቀረ፡፡

በዛሬው እለት የተዋቀረው ብሔራዊ የትግበራ ኮሚቴው ዓላማ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እና ሂደቱን በማመቻቸት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን በኢትዮጵያ ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በስምምነቱ ምክንያት የሚነሱ ተግዳሮቶችንና እድሎችን በመለየት፣ ፖሊሲና ስትራቴጅዎችን በማውጣት የንግድና ኢንቨስትመንት ማደግ ለሀገሪቱ የሚያስገኘውን ፋይዳ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ እና የትግበራውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የሚረዳው ኮሚቴ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ለመተግበር በተዘጋጀው የ2016 በጀት ዓመት ፍኖተ-ካርታ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ እና በሚመራበት የህግ ማእቀፍ ረቂቅ ላይ ተወያይቶ አዳባሪ አስተያየቶችን ሰጥቷል ነው የተባለው፡፡