የአፍሪካ የጤና ኃላፊዎች ከዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ጋር ሊወያዩ ነው

                                              ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

በጤና እና በፋይናንስ ዘርፍ የሚሠሩ የአፍሪካ አመራሮች ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ጋር ስለ ክትባት ሊወያዩ ነው።

የኮሮናቫይረስ ክትባትን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አህጉሪቱ ውስጥ እንዴት ማከፋፈል እንደሚቻል ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዶ/ር ቴድሮስ ከውይይቱ አስቀድመው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “አፍሪካ ውስጥ ክትባቱን ለማሰራጨት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን እንደሆነ እነግራቸዋለሁ። ሕይወት ለማዳንና ምጣኔ ሀብቱ እንዲያገግም ለመርዳትም እንፈልጋለን። የተቀረው ዓለምም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል” ብለዋል።

ከቀናት በፊት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ፤ ሀብታም አገራት የተትረፈረፈ ክትባታቸውን ለድሃ አገራት እንዲያካፍሉ ተማጽነዋል።

የበለጸጉት አገራት ወደ 800 ሚሊየን የሚጠጋ የክትባት ጠብታ ገዝተዋል።

የክትባት ክፍፍልን ፍትሐዊ ለማድረግ የሚሠራው ጋቪ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሴት ቤክሊ እንደሚሉት፤ ይህ ቁጥር ድሃ አገራት ክትባቱን ማግኘት ከመቻላቸው በፊት የበለጸጉ አገራትን ዜጎች ባጠቃላይ ማዳረስ የሚችል ነው።

“ሀብታም አገራት ተጨማሪ 1.4 ቢሊየን ጠብታም አላቸው። ይህ ደግሞ የተለያዩ የክትባት አማራጮችን ያካትታል” ብለዋል።

በበይነ መረብ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ኃላፊው፤ የበለጸጉ አገሮች ያከማቹትን ትርፍ ክትባት ለድሃ አገሮች እንዲሰጡ ለመጠየቅ እንደታሰበ ጠቁመዋል።

“እርዳታ እንዲሰጡ ጠይቀን ካልተሳካልን ክትባቱን ከሀብታም አገሮች እንገዛለን” ሲሉም እቅዳቸውን አብራርተዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ የክትባት ክፍፍሉ ሊፈጥር የሚችለው የሞራል ቀውስ እንደሚያሳስባቸውም ተናግረዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት ዋና የቦርድ አባላት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ኃላፊው፤ በርካታ ሀብታም አገሮች ዓለም አቀፍ የክትባት ክፍፍል ትብብር (ኮቫክስ) አሠራርን መጣሳቸውን ጠቁመዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ እንዳሉት ሀብታም አገራት የኮቫክስ የክትባት ክፍፍል ሂደትን በመጣስ ለዜጎቻቸው ክትባት እያከማቹ ነው። ይህ ደግሞ ድሃ አገራትን ችግር ውስጥ ይከታል።

ሀብታም አገራት ‘ቅድሚያ ለኛ’ በሚል እየሄዱበት ያለው መንገድ ድሃ አገራትና ዜጎቻቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከት ዶ/ር ቴድሮስ አስምረውበታል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።