የአፍ ንፅህና አጠባበቅ

#ጤና_ደጉ

የአፍ ንፅህና አጠባበቅ

በቴዎድሮስ ሳህለ

ሚያዝያ 12/2015 (ዋልታ) በማህበረሰባችን ዘንድ አፍ የሰው ስብዕና መታያ መስኮት ተደርጎ ይወሰዳል። ለዚህም አፍን የተመለከቱ አባባሎቻችን ማሳያ ናቸው። ለምሳሌ አፍ ሲከፈት ማንነት ይታያል (አነጋገርህ ማንነትህን ይገልፃል)፣ አፉን ከፈተ (ተሳደበ/ክፉ ነገር ተናገረ)፣ አፈኛ ነው (ነገረኛ ነው) አፍህን ያዝ (ዝም በል/አትናገር) ከአፍ የወጣ አፋፍ (ምስጢር ከባለቤቱ ከወጣ አበቃለት) ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።

አፍ በአካላዊ ተፈጥሮው የሌላው ውስጣዊ ሰውነታችን መግቢያ በር/መስኮት ነው። ምግብና መጠጥ፣ ጎጂም ይሁን ጠቃሚ ወደ ሰውነታችን የሚገቡት በአፍ በኩል ነው።

አፍ ጤናማ ከሆነ ለሌሎቹም የሰውነታችን ክፍሎች ደህንነት አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው። ሰለሆነም የአፋችንን ጤንነት መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ተግባር ነው። አፍ በራሱ ለራሱ ጤነኛ መሆኑ እንዲሁም ለሌላው የሰውነት ክፍላችን ጤንነት በጣም ወሳኝ በመሆኑ ደህንነቱ ሊጠበቅ ይገባል።

የአፍ ጤንነት ሲባል ምን ማለት ነው?

አፍ ስንል ጥርስን፣ ድድን፣ ምላስን፣ ላንቃን እንዲሁም ከንፈርን ያካትታል።

የአፍ ጤንነት ሲባል የእነዚህ ሁሉ የሰውነት ክፍሎች ጤነኛ መሆን ማለታችን ነው።

ለአፍ ጤና ችግር አጋላጭ ሁኔታዎች፡-

የአፋችን ጤንነት ችግር መንስኤዎች በመሰረታዊነት አኗኗር ዘይቤያችን ነው፤ አደጋና ተፈጥሯዊ መንስኤዎችም ሊሆኑ ይችላሉ።

የአኗኗር ዘይቤያች (life style) ከአፋችን ጤንነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ትምባሆ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጣፋጭ ነገር መመገብና መጠጣት፣ ለጥርስና አፍ ንፅህና ያለን አመለካከት ወዘተ በግላችን ፈልገንና መርጠን የምንከተላቸው የህይወት ዘይቤያችን ናቸው። እነዚህ የዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤ ምርጫዎች በአፋችን ጤንነት በአሉታዊ መልኩ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ጫት እና ትምባሆ አብዝቶ መጠቀም ለአፍ ካንሰር በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ አንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የአፍ ጤንነት አለመጠበቅ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች፡-

➧የጥርስ መቦርቦርና መበስበስ
➧ የድድ መድማትና ማበጥ
➧መጥፎ የአፍ ጠረን ያመጣል
➧የአፍ ውስጥ ቁስለት ያመጣል
➧የምላስ መቆሸሽና የመንጋጋ ማበጥ
➧የጥርስ መነቃነቅ ብሎም መውለቅ ችግር ያመጣል
➧ለሌሎች የውስጥ ደዌ በሽታዎች መከሰት ምክነያት ሊሆንም እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ።

እነዚህ ችግሮች በሰዎች ላይ ሥነ-ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊያስከትሉ እንደሚችሉም በተለያዩ ጊዜያት በወጡ ጥናቶች ተመላክቷል።

የአፍ ጤንነትን እንዴት መጠበቅ ይቻላል፡-

የአፍ ጤንነት በቀላሉ ልንከላከለው የምንችለውና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ተግባር ሲሆን የአፍን ጤንነት ለመጠበቅ መደረግ ያለባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች፦

✔️ ጣፋጭ ምግቦችንና መጠጦችን አለመጠቀም
✔️ ምግብ ከበላን በኋላ ጠዋትና ማታ ጥርስን ፍሎራይድ ባለው የጥርስ ሳሙና መቦረሽ
✔️ አልኮል፣ ጫት እና ትምባሆ ከመጠቀም መቆጠብ
✔️ ጥርሳችንን ስንቦርሽ ምላሳችንን በጥርስ ቡርሽ ከኋላ ወደ ፊት በስሱ መቦረሽ
✔️ የአፍ መጉመጥመጫ ፈሳሽ (mouthwash) መጠቀም (በሃኪም ምክር ቢሆን ይመረጣል)
✔️ የጥርስ ሃኪም በዓመት ሁለት ወይም አንድ ጊዜ ማማከር ይመከራል።

መከላከል ቀላሉ፣ ርካሹናና ምቹ የጤናማነት ዘዴ ነው! (Prevention is the easiest, simplest and cheapest way to be healthy)