በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሚያዝያ 12/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ወንድማማች ሕዝብ መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሠሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠነቀቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓረብኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልእክት የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ በሚገኙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ የሐሰት ውንጀላዎችን በማሰራጨት የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ወገኖች እንዳሉ አመልክተዋል።

እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር አካባቢ ወታደሮቿን አስጠግታለች የሚል የሃሰት መረጃ እያሰራጩ መሆኑንም አንስተው ይህን የወንድማማች ሀገራትን ግንኙነት የሚያሻክር የሃሰት ውንጀላ ኢትዮጵያ በጽኑ እንደምታወግዘው አስገንዝበዋል፡፡

ሁለቱ ወንድማማች አገራት የድንበሩን ጉዳይ በንግግርና በሰላም እንዲሁም በጥሩ ጉርብትና መፍታት እንደሚቻል እኛ ትልቅ እምነት አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ሱዳን ያለችበትን ሁኔታ ኢትዮጵያ በሌላ መንገድ የመጠቀም ዓላማ እንደሌላት ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ አካላት በተለያዩ መንገዶት እንደሚሉት እኛ ይህንን አናደርግም ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ የሱዳን ህዝብም የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደማያምን እምነት አለን ብለዋል፡፡

የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ዓላማም የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ለማጣላት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ እኚህ አካላትም ከዲርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡