የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ 1.7 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ባለፉት ሰባት ዓመታት 1.7 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

ኢንተርፕራይዙ የአዲስ አበባ አዳማ እና ከድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገዶችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በሰባት ዓመታት ውስጥ 46 ሚሊየን ተሽከርካሪዎችን ፍሰት በማስተናገድ 1.7 ቢሊየን ብር ማግኘቱን ገልጿል።

አሁን ላይ በቀን 26 ሺህ ተሽከርካሪዎች የማስተናገድ አቅም ላይ መድረሱንም አመልክቷል።

ኢንተርፕራይዙ ከ300 ኪሎሜትር በላይ የክፍያ መንገዶችን የሚያስተናግድ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ለማዘመንና የሰራተኛውን ምርታማነት ለመጨመር ምቹ የስራ አካባቢ የመፍጠር ስራ መስራቱንም ገልጿል።

በ12 ሚሊየን ብር ወጪ ደረጃውን የጠበቀ መሠብሠቢያ አዳራሽ አስገንብቶ በማጠናቀቅ ለስብሰባ በተለያዩ ከተሞች የሚወጣውን ወጭ መቀነስ መቻሉንም ጠቁሟል።

ኢንተርፕራይዙ በአዲስ አበባ አዳማ የክፍያ መንገድ ጣቢያዎች የሚያገለግል እና ለአረንጓዴ ልማት ስራዎች የሚያግዝ የውሃ የጉድጓድ ቁፋሮ በ6.3 ሚሊየን ብር እያካሄደ መሆኑም ተመላክቷል።

የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎችን ታሳቢ ያደረገና በፍጥነት መንገዱ ለሚገለገሉ አሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ በ57 ሚሊየን ብር ወጪ የነዳጅ ማደያ፣ ማደሪያ ክፍሎች እና መዝናኛዎች ያሉት ሎጅ እያስገነባ መሆኑንም ገልጿል።

ኢንተርፕራይዙ የአየር ብክለትን ለመከላከል በሚያስተዳድራቸው መንገዶች የአረንጓዴ አሻራን ላለፉት ሰባት አመታት እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፣ በዚህ ዓመትም እራሱ ባዘጋጀው የችግኝ ጣቢያ ያፈላውን 212 ሺህ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

(በምንይሉ ደስይበሉ)