የቡሩንዲ የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው አለፈ

የቡሩንዲ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፒየር ቡዮያ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

የ71 አመቱ የቀድሞው መሪ በፓሪስ ህይወታቸው እንዳለፈ ተገልጿል።

በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዳዳንት ቡሩንዲን ለ13 አመታትም ያህል መርተዋል።

በዚህ አመት ጥቅምት ወር የቡሩንዲ ፍርድ ቤት የመፈንቅለ መንግሥቱ ጉዳይ ላይ በተመሰረተ ክስ በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶባቸው ነበር።

ፍርድ ቤቱ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በጎሮጎሳውያኑ 1993 የተመረጡትን ፕሬዝዳንት ሜልቾይር ናዳየን ገድሏቸዋልም በሚል ነው ብያኔውን ያስተላለፈው። በወቅቱም 300 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግን ምንም አይነት ስህተት አልፈፀምኩም በማለት ክደዋል።

በአፍሪካ ህብረት የሳህልን ቀጠና ወክለው ልዩ መልዕክተኛ የነበሩ ሲሆን፣ ባለፈውም ወር ነው ከዚሁ ኃላፊነታቸው የለቀቁት፤ ንፁህነታቸውንም ለማስመስከር እስከ መጨረሻ ድረስ እታገላለሁም በማለት ፀንተው ነበር ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።