የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ

ሚያዝያ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የጀርመን ድርጅት አስተባባሪ ከሆነው (አይ ኤፍ ኢ) ጋር የ1.2 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የጀርመኑ ማስተባበሪያ ቢሮ ኮርፖሬሽኑ የያዘውንና ግዙፍ ሀገራዊ አላማ የሆኑትን የስራ እድል ፈጠራን መጨመር፣ የውሀ አቅርቦት ተደራሽነትን ለማሳደግ እንዲሁም የአምራች ኩባንያዎች አቅም ማሳደግና እርካታን ለመጨመር በመተባበር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ በሙሉ አቅም ተግባራዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ አረጋግጠዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተፈራረመው ስምምነት በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የንፁህ ውሀ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ የአምራች ኩባንያዎችን እርካታ በመጨመር ፓርኩ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ እና ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ያለመ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ነው መባሉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።