የሳተላይት መረጃዎችን በመጠቀም የምርምር ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተገለጸ


ሚያዝያ 9/2016 (አዲስ ዋልታ) የሳተላይት መረጃዎችን ለተቋማት ተደራሽ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እንዲጎለብቱ እየተሰራ መሆኑን የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በጂኦ-ስፓሻል ዘርፍ መረጃ ለተቋማት ተደራሽ ማድረግ በሚያስችለው ሁኔታዎች ላይ ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቤተልሔም ንጉሴ ኢንስቲትዩቱ ለአምስት ዓመታት የሳተላይት መረጃዎችን ለማግኘት ከቻይና የተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ጋር ሥምምነት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ይህንም ተከትሎም አሁን ላይ የሦስት ሳተላይቶች መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ወደ መረጃ ቋት እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ኢንስቲትዩቱ እነዚህን መረጃዎች በመጠቀም የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለሌሎች ተቋማት የሳተላይት መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የምርምር ሥራዎች እንዲጎለብቱና የልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ በትኩረት እየሰራ ነውም ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የሪሞት ሴንሲንግ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ብርሃን ገሠሠ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሳተላይት መረጃዎችን ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና ተያያዥ ሥራዎች መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል።

ለአብነትም የሰብል ምርትን ለማሳደግ፣ የእንስሳት ልማትን ለማጠናከርና የተፈጥሮ አደጋዎችን የመከላከል ተግባራትን ለማከናወን የሳተላይት መረጃዎች ወሳኝ እንደሆኑ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመሆኑም ተቋማት ከኢንስቲትዩቱ ጋር ሥምምነት በመፈጸም የሳተላይት መረጃዎች ማግኘት
እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።