የኢጋድ ቀጠናዊ የካንሰር ልህቀት ማዕከል የማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ቀጠናዊ የካንሰር ልህቀት ማዕከል ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የጤና ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንዲሁም የኢጋድ አባል ሀገራት አምባሳደሮች ተገኝተዋል::
በአውሮፓዊያኑ 2012 በኢጋድ ምክር ቤት ውሳኔ የተቋቋመው ማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካንሰርን ለመዋጋት ቁልፍ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ፕሮጀክቱ በካንሰር ለሚሰቃዩ ዜጎች ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ እና ለስኬታማነቱም ሁሉም አካል ቁርጠኝነት ያለው አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ ሲጠናቀቅ የምርመራ፣ ህክምና እንዲሁም ጥናትና ምርምርን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ያለው የካንሰር እንክብካቤ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ አክለዋል፡፡
የማዕከሉ ዋና ዓላማ በቀጠናው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን ከካንሰር ጋር የተያያዙ የጤና አጠባበቅ ችግሮችን ለመቋቋም፣ የካንሰር በሽታን ለመከላከል እና ለማከም ብቁ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ለማዕከሉ ግንባታ ከሊዝ ነፃ የሆነ 20 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልፀው፣ ግንባታው በተፋጠነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ቀን እና ለሊት ለመስራት የሚያስችል አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ እንዲመቻቹ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
የማዕከሉ ግንባታም 500 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ ተገልጿል፡፡
(በአመለወርቅ መኳንንት)