ጠቅላይ ዐቃቤሕግ እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች በአማራ ክልል የበጎ አድራጎት ስራዎችን አከናወኑ

ሐምሌ 21/2013(ዋልታ) – የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የሰነዶች ማረጋገጫ ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ የግብር ይግባኝ ኮሚሽን፣ የፍትህ ምርምር ኢንስቲቲዩት፣ የአምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት እና የሲቪል ማህበራት ኤጀንሲ አመራሮች በአማራ ክልል  ሞጣ ከተማ  ስምንት የሚሆኑ የአቅመደካማ ቤቶችን አፍርሶ የማደስ ስራ እንዲሁም ከተማዋ ላይ የጽዳት ዘመቻ ያካሄዱ ሲሆን በምስራቅ ጎጃም ዞን በእጁ እነሴ ወረዳ  በአዲስ ዘመን ቀበሌ ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርን ተከትሎ በቀበሌዋ ከወረዳው አመራሮችና ማህበረሰቦች ጋር በመሆን 5ሺ ችግኞችን ተክለዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌድሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ(ዶ/ር) ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀው በዋናነት የህዝቡን አንድነት ለማጠናከርና የአረንጓዴ ልማት አሻራን እንዲሁም የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለማጠናከር መሆኑን ገልጸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችም ስኬቱን ለማጠናከር ሲባል የድርሻችንን ለመወጣት እዚህ ተገኝተን እነዚህን ተግባራት አከናውነናል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ይህ ተግባበር አመት በአመት የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው የአካባቢው ማህበረሰብ ስላደረገልን አቀባበል ማመስገን እፈልጋለሁ እንግዳ ተቀባይነታችሁንም በተግባር አሳይታችሁናል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ አመራሮች በበኩላቸው በክልላችን ተገኝታችሁ ይህን ተግባር ስላከናዎናችሁ እናመሰግናለን ይህ በአልም ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል አንድነትን ለማጠናከርና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማዳበር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የወረዳው አስተዳደርም ስለተከናዎኑት ተግባራት አመስግነው የተከላችሁትን ችግኞች ከአካባቢው ማህበረሰብና ከገበሬዎቻችን ጋር በመሆን ተንከባክበን አጽድቀን እናሳያችዋለን መጥታችሁ አሻራችሁን ስላስቀመጣችሁም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡