የአሸባሪው ጁንታ ግፍ በታዳጊዋ ሳራ አደም አደበት-ከአፋር ጦር ግንባር

ሳራ አደም ትባላለች፡፡ ትውልዷ አዲግራት ከተማ ነው፡፡ እድሜዋ 16 እንደሆነና ገና 10ኛ ክፍል እንዳልጨረሰች ገልፃለች፡፡ ከእናት እና አባቷ ቤት የወጣችው ስልጠና አለ ተብላ ነበር፡፡

(በደረሰ አማረ ከአፋር ጦር ግንባር)
ሳራ አደም ትባላለች፡፡ ትውልዷ አዲግራት ከተማ ነው፡፡ እድሜዋ 16 እንደሆነና ገና 10ኛ ክፍል እንዳልጨረሰች ገልፃለች፡፡ ከእናት እና አባቷ ቤት የወጣችው ስልጠና አለ ተብላ ነበር፡፡ ከ4 የቅርብ ጓደኞቿ ጋር ስልጠና ወደተባለበት የካቲት ከፍለ ጦር ውስጥ ታዳጊዋን ቀላቀሏት፡፡ በሰዓቱ በአንድ ሺ አለቃ ስር 60 ልጆች ነበርን፡፡ ከ60ዎቻችን ውስጥ መሳሪያ እኔን ጨምሮ ያልተሰጠን እንዳለ ሁሉ የያዙም ልጆች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ የኔ እኩዮች ናቸው፡፡ ከአዲግራት ከመጣነው ውስጥ የማውቃቸው 4ቱን ጓደኞቼን ነው፡፡ ከእነርሱ መካከል ሁለቱ በሌላ ግንባር ነው የተወሰዱት፡፡ ፌበን ገብሬ ከምትባለው ጓደኛዬ በአንድ ጦር ግንባር ነበርን፡፡ ሁለት ሳምንት ያህል በየካቲት ክፍለ ጦር እንድንቆይ ተደረግን ትላለች፡፡

ከሁለት ሳምንት ቆይታ በኋላ ምንም ወደማናውቀው አካባቢ ነበር ያመጡን። በኋላም አንድ ስፍራ አራገፉን፤ ከዚህ በኋላ ያለው አፋር ክልል ነው፡፡ ወደ ክልሉ ዘልቃችሁ በመግባት ትዋጋለችሁ ብለው ሰደዱን፡፡ ያመጡን ሰዎች ከኋላችን ቀሩ፤ ውጊያ ገጠምን በኋላ ግን ብዙም ሳንቆይ ተመታን። ጓደኛዬ ፌበን ገብሬ ወዲያው ህይወቷ አለፈ፡፡ ሌሎችም ሞተዋል፡፡ እኔ ግን እጄንና ዳሌ ላይ ነው በጥይት የተመታሁት፡፡ መንቀሳቀስ ከበደኝ፡፡ አብረውኝ የነበሩትን ከስፍራው እንዲያወጡኝ ስጠይቃቸው እጄን ብቻ አሰሩልኝና ሁሉም ጥለውኝ ወደ ኋላ ሸሽተው ሮጡ፡፡ ሲያዋጉኝ የነበሩ የምትላቸው ስሙን ግን የማታውቀው አንድ መሳሪያ የያዘ ሰውዮ አጠገቧ እንደነበረ ታስታውሳለች፡፡ ከዚህ አውጡኝ ብዬ ለመንኩት፤ ምንም ምላሽ ሳይሰጡኝ ጥለውኝ ሮጠው ሸሹ ትላለች ሳራ፡፡ ከዚያ ስፍራ ብዙ ደም ፈሰሰኝ፡፡ በኋላ አንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል መጥቶ ደግፎኝ አወጣኝ፣ የሚጠጣም፤ ህክምናም እንዳገኝ አደረገኝ፡፡

ከተማረኩ በኋላ መከላከያ ሰራዊቱ ህክምና እየሰጠኝ ይገኛል፡፡ ለትግራይ እናቶች የምመክረው ነገር ልጆቻቸውን ጥቅም አልባ ለሆነው ጦርነት እንዳይሰጡ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቻችን ጋር ተጋጭተን በማንወጣውና ጥቅም በሌለው ጦርነት በየበረሀው እየቀረን ነው፡፡ ይህ ጦርነት ቢቀርስ መልካም ነው ስትል መልዕክት አስተላልፋለች፡፡

ገብረሚካኤል ሀፍቱ የተባለውም ታዳጊ ደግሞ ልክ እንደ ሳራ ሁሉ በጁንታው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተታሎ ነበር ከማይጨው ወደ ጦር ግንባር የከተመመው፡፡ ገብረሚካኤል እንደ ሳራ የካቲት ክፍለ ጦር የመግባት እድል አላገኘም፡፡ ከማይጨው ከእናትና አባቱ ቤት ካስወጡት በኋላ በየ ተራራውና በየ ገደሉ ጁንታው ይዟቸው ይጓዝ እንደነበረ ተናግሯል፡፡ በየገደላ ገደሉ ለምን እንሄዳለን? ብለን ስንጠይቃቸው ስልጠና እኮ እየሰለጠናችሁ ነው ይሉን ነበር ይላል፡፡ ውጊያ ሊያስገቡን እንደሆነ ያወቅነው፤ አፋር ክልል ላይ ከደረስን በኋላ አሁን ትዋጋላችሁ ሲሉን ነው ሲልም ያክላል፡፡

ከዚያ በኃላ እኛም ምርጫ አልነበረንም። ወደ ጦርነት ገባን። እነርሱ ግን ወደ ኋላ ተመለሱ፡፡ ከጥቂት የውጊያ ቆይታ በኋላም በጦርነቱ መቁሰሉንና በሀገር መከላከያ ሰራዊት መማረኩን ገብረሚከካኤል ይናግሯል፡፡ በቂ ህክምና ማግኘቱንም ገልጿል፡፡

ሁለቱም ባለታሪኮቻችን በውጊያወ ክፉኛ ስለቆሰሉ ህክምና እየተከታተሉ ናቸው፡፡