የኤርታሌ ሰሜናዊ ክፍል ከ50 ዓመታት በኋላ የእሳተ ጎመራ ጉድጓድ በመፈንዳት ዳግም የቅልጥ አለት ሀይቅ ፈጠረ

ጥር 25/2015 (ዋልታ) የኤርታሌ እሳተ ጎመራ ሰሜናዊ ክፍል የእሳተ ጎመራ ጉድጓድ በመፈንዳት ከ50 ዓመታት በኋላ የቅልጥ አለት ሀይቅ መፈጠሩ ተገለፀ፡፡
በአፋር ክልል በደናክል ዝቅተኛ ቦታዎች ውስጥ በሚገኘው ኤርታአሌ የእሳተ ገሞራ ቆሪ (ካልዴራ) ትልቅ የቀለጠ አለት ኃይቅ መፈጠሩ ተመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1967 ዓ.ም በእሳተ ገሞራ አጥኝ ባለሙያዎች የደቡባዊ እና ሰሜናዊ ቅልጥ አለት ኃይቆች ሞኖራቸውን ካረጋጡ በኋላ በ1974 የሰሜኑ ኃይቅ የቀለጠው ፈሳሹ በመጥፋት ጭስ ብቻ ሆኖ የእሳተ ገሞራ ቆሪ (ካልዴራ) መፈጠሩን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከ50 ዓመታት በኋላ ግን አርብ ጥር 19/2015 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜናዊ የኤርታ አሌ ክፍል የእሳተ ጎመራ ጉድጓድ በመፈንዳት ዳግም የቅልጥ አለት ሀይቅ መፍጠሩን ቮልካኖ ዲስከበሪ በይፋዊ ገፁ ላይ አስታውቋል፡፡
ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጅኦፊዚክስ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተመራማሪ አታላይ አየለ (ፕ/ር) ስለ ክስተቱ መረጃ እንዳላቸው ገልፀው በተመሳሳይ እ.ኤ.አ 2017 የኤርታሌ ደቡባዊ ክፍል በቅልጥ አለት ተሞልቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የጅኦቱሪዝም ባለሙያ እንቁ ሙሉጌታ ክስተቱን በቦታው ላይ ተገኝተው መመልከታቸውን ሲገልፁ በዓለም ላይ እንዲህ ያለ የእሳተ ጎመራ ክስተት ከፍተኛ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስብ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

የአፋር ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አህመድ አብዱርቃዲር የኤርታሌውን አዲስ ክስተት ለመጎብኘት በርካታ ቱሪስቶች ፈላጎት ማሳየታቸውን ገልጸው በጦርነት የተዳከመ የአከባቢውን ቱሪዝም ፍሰት ለማነቃቃት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ