የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ህገ ወጥ የመሬትና ሌሎች ግኝትቶች ላይ የውሳኔ ሃሳብ አስተላለፈ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው ስብሰባ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ ባለቤት አልባ ህንፃዎች፣ የኮንደሚኒየም ቤቶች፣ የቀበሌ መኖሪያና ንግድ ቤቶችን አስመልክቶ በጥናት የተገኘው ግኝትቶች ላይ የውሳኔ ሃሳብ አስተላለፈ፡፡

የከተማው ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የከተማው አመራር በሪፎርሙ በገባው ቃል መሰረት ምንም እንኳ ቢዘገይም የነዋሪው ቅሬታ መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት እና በተጨባጭ ጥናት በመመርኮዝ ለማጣራት እና ለመለየት የተደረገውን ጥረት ያመሰገኑ ሲሆን፣ ወደፊት መወሰድ አለበት ባሉት እርምጃ ላይ አፅንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል፡፡

በመሆኑም በጥናቱ የተገኙ 322 ባለቤት አልባ ህንጻዎች በግልፅ ጨረታ ተሽጠው ወደ መንግስት ካዝና ገቢ እንዲሆኑ፣ በጥናቱ የተገኘው ህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ ባዶ ሆነው የተገኙ 21,695 የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በማስለቀቅ ለተጠቃሚዎች እንዲታደል፣ በዋናነት በ1997 ተመዝጋቢ የሆኑና በቋሚነት እየቆጠቡ ላሉ ነዋሪዎች በእጣ እንዲተላለፍ፤

የቀበሌ ቤቶችን አስመልክቶ በህገ-ወጦች የተያዙ የመኖርያ ቤቶች ግልፅ የሆነ መስፈርት ወቶላቸው ለደሆች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለተለያየ ችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎች እንዲሰጥ፤፣

የቀበሌ የንግድ ቤቶች በህገ-ወጥነት ከያዙት ሰዎች ተነጥቆ ለስራ አጥ ወጣቶች በእጣ እንድሰጥ ሲሉ መወሰናቸውን የአስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሪታሪያት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ካቢኔው በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በሰፊው የተወያየ ሲሆን፣ ይህ ችግርና ስርዓት አልበኝነት 1997 ዓ.ም ጀምሮ እየተንከባለለ የመጣ መሆኑን እና ወደፊት እንዳይደገም በፅናት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡