የሕግ ማስከበሩን ሁነቶች የሚያሳይ “ዘመቻ ለፍትህ” የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ተከፈተ

በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚያሳይ “ዘመቻ ለፍትህ” የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተከፈተ።

በአውደ ርዕዩ መክፈቻ የህወሓት ጁንታ የፈፀማቸው ጥፋቶች ተሰንደው ለትውልድ መማሪያ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተዘጋጀው “ዘመቻ ለፍትህ” የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል።

አውደ ርዕዩን የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሪል አድሚራል ክንዱ ገዙ፣ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አወሉ አብዲ፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰና የሚዲያዎች አመራሮች ከፍተውታል።

መከላከያ ሰራዊት በሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የፈጸማቸውን ተጋድሎዎችና ጀብዱዎች እንዲሁም የህወሓት የጥፋት ቡድን የፈጸማቸውን ዒ-ሰብዓዊ ድርጊቶች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ለዕይታ ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞች በግንባር ተገኝተው የዘገቧቸው የህትመት ውጤቶችም እንዲሁ።

የጥፋት ቡድኑ የፈጸመው ድርጊት መጥፎ ጠባሳ ጥሏል ያሉት ሪል አድሚራል ክንዱ ታሪክ ጥሩ ጥሩው ብቻ ስላይደለ መጥፎ ታሪካችን ዳግም እንዳይከሰት ለትውልድ ማስተማሪያ በሚሆን መልኩ ሰንዶ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ወቅታዊና ጠቃሚ መሆኑን አውስተዋል።

በጁንታው የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት በፎቶግራፍ አውደ ርዕይ የሚያበቃ አይደለም ያሉት አድሚራል ክንዱ የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሃፊዎች ጉዳዩን በትኩሱ በመጻፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው ሰራዊቱ የተፈጸመበትን የግፍ ጥቃት በመመከት ለድል መብቃቱ ለአገር የሚከፈል መስዋዕትነት ምን ማለት እንደሆነ አስተምሯል ይላሉ።

የጥፋት ሃይሉ ለጦርነቱ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጅበት መቆየቱን አስታውሰው በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያዊያን መሸነፉ ኅብረት ካለ ጥሩ ውጤት እንደሚኖር ማሳያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በግንባር ተገኝተው እውነትን የማፈላለግ ተልዕኮ ጭምር በመወጣት ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አንስተዋል።

ድርጅቱ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት አስመልክቶ የተለያዩ ሁነቶችን እያካሄደ ሲሆን አውደ ርዕዩም የዚሁ አካል መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በቅርቡ በሕግ ማስከበር ዘመቻ በተለያዩ ግንባሮች ተሰማርተው በሙያቸው ላገለገሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እውቅና መስጠቱም ይታወሳል።