የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል በመመረያ ቁጥር 30 የተቀመጡ የክልከላ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገለፀ

መጋቢት 18/2013 (ዋልታ) – አሳሳቢ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ከዚህ ቀደም በመመረያ ቁጥር 30 የተቀመጡ የክልከላ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ የጤና ሚኒስቴር እና የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቁ።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እጅጉን በመስፋፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በሌላ በኩል በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታየው ቸለተኝነትና መዘንጋት ችግሩን ወደ ከፋ ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል። ከዚህ ቀደም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጠር ስርጭቱንም ለመግታት የሚያግዝ መመሪያ ቁጥር 30 መውጣቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን አተገባበሩ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይስተዋላል ነው የተባለው።
በመመሪያው የተቀመጡ የክልከላ እርምጃዎችን ተከታትሎ ማስተግበር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል። ስለሆነም የጤና ሚኒስቴር፣ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤህግና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ይኸው ተግባራዊ እንዲሆን በጋራ ለመስራት መግለጫ ሰጥተዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው እንደተመላከተው ማንኛውም ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ወደ ማህበረሰቡ እንዳይቀላቀል እንዱሁም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ቫይረሱ ሊተላለፍ በሚያስችል ሁኔታም ንክኪ ማድረግ በህግ የሚያስቀጣ ይሆናል::
በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳይደርግ መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን የንግድና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ሰጪውም ሆነ አገልግሎት ተቀባይ ማስክ ሳያደርግ መስተናገድ ክልክል ነው ።
ማንኛውም የሚደረጉ ስብሰባዎች በመመሪያው የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላ ስለመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፣ አስፈላጊ እርምጃም ይወሰዳል።
መመሪያውን ተግባራዊ በማያደርጉ አካላት ላይም አስፈላጊው የቅጣት እርምጃዎች እንደሚወሰድ ጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጹን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።