ጽንፈኛ ብሄረተኝነት  በሀገሪቱ የፈጠረውን አደጋ እናሸንፈዋለን- አቶ አገኘሁ ተሻገር

አቶ አገኘሁ ተሻገር

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – ጽንፈኛ ብሄረተኝነት  በሀገሪቱ የፈጠረውን አደጋ እናሸንፈዋለን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ  መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በባህርዳር ከተማ አካሂዷል።

በቅስቀሳ መርሃ ግብሩ ፓርቲው  ማኒፌስቶውን፣ መወዳደሪያ ምልክት እና ዕጬዎችን አስተዋውቋል።

በምርጫ  ቅስቀሳ ፕሮግራሙ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አገኘሁ  ተሻገር፣ ብልጽግና በአማራ ህዝብ  ለዘመናት የተፈጸመበትን ሴራ ያስወገደ ፓርቲ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የዘንድሮው ምርጫ ሀገሪቱን እና ህዝቦቿን ከከበበው መከራ የምንወጣበት እና ወደ ብልጽግና የምንጓዝበት ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

በርካታ ፈተናዎች እንደ ሀገር እና በክልላችን የተጋረጡ ቢሆንም፤ ይህንን ችግር በብልጽግና እሳቤ እናልፈዋለን ሲሉም አክለዋል፡፡

የአማራ ህዝብ በማንነቱ የሚደርስበትን ፈተና እና ሰቆቃ እንደ ሀገር ሁላችንም ተባብረን ልንፈታው ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሀገሪቱን እና አማራ ክልልን ለማፍረስ የሚጥሩ ሀይሎችን እናፈርሳቸዋለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የባለሀብቶች፣ የምሁራን እና የሁሉም ነው ሲሉ አመልክተዋል።

ፅንፈኛ ብሄርተኝነትን በማሸነፍ ህብረ ብሄራዊነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፣ በሀገሪቱ የፈጠረውን አደጋም እናሸንፈዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ የትኛውንም መስዋትነት እንከፍላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ፣ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ ሀይሎች አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንም የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

(በየሻምበል ባምላኩ)