የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው መመሪያ በአፈፃፀም ክፍተት ተግባራዊ አልሆነም ተባለ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያ በፖሊስና በዓቃቤ ሕግ የአፈፃፀም ክፍተት እየተተገበረ እንዳልሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገለፀ።

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጉዳትና ስርጭት ለመቀነስ የተጣሉ ክልከላዎችና ግዴታዎችን በሕግ ለመወሰን የሚያስችል መመሪያ አውጥታለች።

የወጣው መመሪያ 30/2013 ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር ነው።

በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተመዘገበ ይህ መመሪያ ክልከላውን የጣሰ ማንኛውንም ግለሰብና ተቋም አግባብነት ባለው የወንጀል አንቀጽ እንደ ጥፋቱ መጠን እንዲቀጣ የሚያደርግ ነው።

ኢዜአ መመሪያው ስራ ላይ እንዲውል ከተደረገ ጀምሮ የነበረውን አፈጻጸም፣ አተገባበርና የባለድርሻ አካላትን ሃላፊነት አስመልክቶ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ጋር ቆይታ አድርጓል።

ክልከላዎችና ግዴታዎችን ያልተወጣ ግለሰብም ሆነ ተቋም በወንጀል እንደሚጠይቅ ቢደነግግም በፖሊስና በአቃቤ ሕግ ቸልተኝነት መመሪያው ተግባራዊ አልሆነም።

መመሪያው ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ ግለሰብና ተቋም ላይ የሚወሰዱ ቀጥተኛ ቅጣቶችን ዘርዝሮ ባለማስቀመጡ ሕግ አስከባሪዎች ቸል እንዲሉ ማድረጉንም አንስተዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሰዎችን ከመክሰስ ይልቅ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ስለ መመሪያው ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ቢያተኩርም ለውጥ አለመምጣቱን ነው አቶ አወል የጠቆሙት።

አቃቤ ሕግና ፖሊስ በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎችና ግዴታዎችን ከማክበር ይልቅ ቸልተኝነቱ እየተባባሰ በመምጣቱ መመሪያውን ያላከበሩትን ተጠያቂ የማድረግ ግዴታ አለባቸው ብለዋል።