የኮንታ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው

የኮንታ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – የኮንታ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በአመያ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኮንታ ልዩ ወረዳ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤት ያዘጋጀው ሲምፖዚየሙ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የልዩ ወረዳው ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ላይ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል፡፡

በሲምፖዚየሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታሁን ብላቴ የልዩ ወረዳው ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ሳይበረዝ የዘመነ ሉላዊ ተፅዕኖን ተቋቁሞ የህዝቡን እሴት ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ መሆኑን በጥልቀት በመገንዘብ ሲምፖዚየሙ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት የሆነው የኮንታ ልዩ ወረዳ ያለውን እምቅ ሀብት በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሳቢያ በሚፈለገው ደረጃ ማልማት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙ የአካባቢው ተወላጆች፣ ምሁራንና የኮንታ ወዳጆች በሙሉ የልዩ ወረዳውን ሀብት ለማልማት አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት መድረክ እንዲሆን ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በልዩ ወረዳው ከ300 ሺህ በላይ ህዝብ እንደሚኖር የሚጠቀስ ሲሆን፣ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች ይገኙበታል፡፡

የገበታ ለሀገር የኮይሻ ፕሮጀክትና የኮይሻ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ የሚገነባበት አካባቢ መሆኑም ይታወቃል፡፡

ሲምፖዚየሙ ከግንቦት 10 እስከ 11/2013 ዓ.ም እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል፡፡

(በሳሙኤል ሀጎስ)