ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ተገለጸ

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ያላትን ፍላጎት ማሳየቷ ተገለጸ።
በኩባ የኢትዮጵያ ባለሙሉስልጣን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኩባ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንቫይሮመንት ሚኒስትር ፔርዝ ሞንቶያ ጋር አገሮቹ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ስለሚሰሩባቸው ጉዳዮች ምክክር አካሂደዋል።
በቆይታቸው ኢትዮጵያና ኩባ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ የተዳሰሰ ሲሆን በባዮቴክኖሎጂ፣ በሜትሮሎጂና ሥነ ፈለክን ጨምሮ በሌሎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትብብር ጉዳዮች ላይም መክረዋል፡፡
በዚህ ወቅት አምባሳደር ሽብሩ ስለመጪው ምርጫና ይዞ ስለሚመጣው ሰፊ እድል፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተካሄዱ ያሉ ድርድሮችን፣ የኢትዮ ሱዳን ድንበርን በተመለከተ እንዲሁም በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስለሚገኘው የሰብአዊ ድጋፍ እና የመልሶ ግንባታ ተግባራት ገለጻ አድርገዋል።
የኩባ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንቫይሮመንት ሚኒስትር ፔርዝ ሞንቶያ በበኩላቸው በርፉ ላይ የኩባና የኢትዮጵያ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን የቨርቹዋል ምክከር ለማዘጋጀት ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።