ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – በኦክስፎርድ የኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እና በቡርኪናፋሶ ሳይንቲስቶች በጋራ የተሰራ አዲስ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት በተደረገለት ሙከራ ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ።
በክትባቱ ላይ በተደረጉት መጀመሪያ ሙከራዎች 77 በመቶ በሆነ ውጤት ስኬታማ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ይህም አሁን ለህክምና ከሚውሉ መድኃኒቶች አንጻር ውጤታማነቱ በእጅጉ የላቀ ነው ተብሏል።
የህክምና ጉዳዮች መጽሔት በሆነው ‘ላንሴት’ ላይ የታተመው የጥናቱ ውጤት 450 ከቡርኪናፋሶ የተወጣጡ ህጻናት የተሳተፉበት ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በርከት ያሉ ሰዎች የሚሳተፉበት ሙከራ ይደረግበታል ነው የተባለው።
በቀጣዩ የሙከራ ሂደትም 4,800 ህጻናት የሚሳተፉ ሲሆን፣ እነዚህም ከቡርኪናፋሶ፣ ከማሊ እና ከኬንያ መሆናቸው ተጠቁሟል።
“ይህ ሙከራ በጣም አስደሳች የሆነ ውጤታማነት እንዳሳየና ክትባቱ ከዚህ በፊት ከነበሩ ህክምናዎች አንጻር የተሻለ የመከላከል ብቃት ማሳየቱ ተገልጿል።
በቡርኪናፋሶ የጤና ሳይንስ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሃሊዶ ቲንቶ “በመቀጠል የምናካሂዳቸውን ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ሙከራዎች እየተጠባበቅን ነው፤ በእነዚህ ሙከራዎች በርከት ያሉ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ በስፋት ቢመረት ምን አይነት ውጤት እንደሚኖረው ለማወቅ ይረዳናል” ብለዋል።
ለወባ በሽታ የሚሆን ክትባት ማግኘት በህክምና ምርምር ውስጥ እግጅ ትልቅ ዜና ሲሆን፣ ሙከራው በስኬት የሚጠናቀቅ ከሆነ ትልቅ ግኝት እንደሚሆንም ይጠበቃል።
የወባ በሽታ በዓመት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎችን የሚገድል ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ከሰሀራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ህጻናት ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ ለወባ በሽታ የሚሆን አንድ ክትባት ያለ ሲሆን፣ ውጤታማነቱ ደግሞ 50 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል።
በአዲሱ ክትባት የመጀመሪያ ዙር ሙከራ ላይ 77 በመቶ ውጤታማነት የታየ ሲሆን፣ በሌሎች አገራትም ላይ ለመሞከር ታቅዷል። በጊዜ ብዛት ደግሞ ቢያንስ በአራት የአፍሪካ አገራት ውስጥ ይሞከራል ነው የተባለው።
በሙከራው የሚሳተፉት 5 ሺህ የሚሆኑ ህጻናት ደግሞ እድሜያቸው ከሦስት ዓመት በታች የሆኑ ናቸው።
አሁን በሙከራ ላይ የሚገኘው አዲሱ ክትባት ሙሉ ፈቃድ አላገኘም። ነገር ግን ውጤታማነቱ በሙከራዎች በተገቢ ሁኔታ የሚረጋገጥ ከሆነ የበርካቶችን ህይወት የማትረፍ ትልቅ አቅም አለው መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል።