የዓለም ባንክ ለትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

መጋቢት 2/2013 (ዋልታ) – የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም በሚከናወነው ተግባር ዓለም ባንክ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኦስማኔ ዲሆኔ ገለጹ፡፡

በትግራይ ጉብኝት ያደረጉት ዳይሬክተሩ ከክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል፡፡

ባንኩ ከዚህ በፊት ለክልሉ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት የባንኩ ተጠሪ፣ አሁንም ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

“ባንኩ በክልሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና ሰብዓዊ አቅርቦቱን ለማገዝ ዝግጁ ነው” ብለዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊ የነበሩት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሪት ያስሚን ወሃብረቢ በበኩላቸው፣ መንግስት ክልሉን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፌዴራሉ መንግስት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን፣ የመንግስት ተጠሪ ተቋማትን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ አገር በቀል ድርጅቶችንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማስተባበር ክልሉን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በበኩላቸው፣ በክልሉ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ጠቁመው፤ ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ከመንግስት በተጨማሪ የሌሎች አካላት ሰፊ እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ ምዕራባዊና ደቡባዊ ዞን ለተፈናቀሉ 700 ሺህ ሰዎች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ክልሉ የራሱን በጀት እያመነጨ ባለመሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናከሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡