ሐምሌ 30/2013 (ዋልታ) – የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎሳ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ የካቢኔ ለውጥ ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከሦስት አመት በፊት የአገሪቱን መንበረ ስልጣን በምርጫ ከተረከቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የደቡብ አፍሪካን ከፍተኛ ስራ አስፈጻሚዎች ለውጥ እንዳደረጉ አናዷሉ አስነብቧል።
የካቢኔ ለውጥ ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የአገሪቱ የጤና፣ የገንዘብ፣ የመከላከያና የወታደራዊ ጉዳዮች፣
የኮሚኒኬሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ የህዝብ አስተዳደርና የቱሪዝም ሚኒስቴር ይገኙበታል።
ከዚህ ባለፈ የካቢኔ ለውጡ ምክትል ሚኒስትሮችንም እንደሚያካትት ተገልጿል።
በደቡብ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከኮቪድ -19 የክትባት መርሃ ግብር የማፋጠን ፍላጎትን ለማሳካት፣ ኢኮኖሚውን እንደገና ለመገንባትና የቅርብ ጊዜ ሁከቶችን ተከትሎ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ብሎም በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ የካቢኔ ለውጡ አስፈላጊ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
እነዚህን ተግባራት በብቃት ለማከናወንና የመንግስትን አቅም ለማሻሻል በብሔራዊ አስፈፃሚው ላይ ለውጦችን እያደረግኩ ነው ማለታቸውን የደቡብ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።