“የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ” ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ ተገለጸ

ግንቦት 17/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ጠንካራ የግል መረጃ ጥበቃ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችልና ግልሰቦች በግል መረጃቸው ላይ ያላቸውን ዝርዝር መብትና ጥበቃ የሚደነግግ “የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ” ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ አዋጅ በኢትዮጵያ የግል መረጃ ጥበቃ ስርዓት አለምአቀፋዊ ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ የግል መረጃ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ሀገር፣ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውሥጥ በማዘዋወር መልካም እድሎችን አሟጦ መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡
አዋጁ በህገ መንግስቱ የተደነገገውን የግል መረጃ ጥበቃ ተመርኩዞ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።
የሰዎች የግል መረጃ የማቀናበር መርሆዎች ባለመቀመጣቸውና የግል መረጃ ተቆጣጣሪ አካል ባለመሰየሙ በኢትዮጵያ ጠንካራ የግል መረጃ ጥበቃ ስርዓት ሳይዘረጋ ቆይቷል።
አዋጁ የማንኛውም ግለሰብ መረጃ ሲቀናበር የግላዊ መብቱን ባከበረ መልኩ እንዲሆን የሚደነግግና ጥንቃቄ የሚፈልጉ መረጃዎችን ማቀናበርን የሚከለክል መሆኑም ተገጸዋል፡፡
ለህክምና አላማ ተፈልጎ በሃኪም ቤት ከተከናወነና በፍርድ ሂደት ከተወሰነ ማቀናበርን የሚፈቅደው አዋጁ በኢትዮጵያ ጠንካራ የግለሰብ መረጃ ጥበቃ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል ነው የተባለው።
ለየትኛውም አላማ የተቀናበረ የግለሰብ መረጃ አስፈላጊ ከሆነበት ጊዜ በላይ መቀመጥ እንደሌለበት የሚደነግገው አዋጁ መረጃውን የሰበሰበው የተፈቀደለት አካልም መረጃውን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ለመስጠት በ3ኛ ወገን የስልጣን ክልል ውስጥ ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግ ሲያረጋግጥ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል።
ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል መረጃን ከሀገር ውጪ ለማስተላለፍ በቅድሚያ የኮሚሽኑን ፍቃድ ማግኘት እንደሚያሰፈልግም ተገልጿል፡፡
አዋጁ የዲጂታል ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ታዕማኒ የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር ግለሰቦች ከደህንነት ስጋት እንዲላቀቁ ያስችላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
(ምንጭ፡- ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)