የግርማ የሺጥላ አላግባብ መሰዋት ከብልጽግና ጉዟችን እና አላማዎቻችን የሚያቆመን ሳይሆን ይበልጥ የሚያበረታን ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሚያዝያ 23/2015 (ዋልታ) የግርማ የሺጥላ አላግባብ መሰዋት ከብልጽግና ጉዟችን እና አላማዎቻችን የሚያቆመን ሳይሆን ይበልጥ የሚያበረታን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል በሆነው ሀላላ ኬላ ሪዞርት ምርቃት ወቅት ባደረጉት ንግግር አቶ ግርማ የሺጥላ ህይወታቸው እስካረፈበት ወቅት ድረስ ለህዝቦች ወንድማማችነትና አንድነት ሮጠው ያልጠገቡ ናቸው ብለዋል።

በሃሳብ ብልጫ መሻትን ማሳካት እየተቻለ ነገር ግን በዚያ መንገድ ፍላጎታቸውን ማሳካት የተሳናቸው ጀግና መሳይ ፈሪዎች የወንድማችንን ህይወት ነጥቀዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፡፡

ዘመኑ የሚፈቅደው ሀሳብ በማመንጨትና ለብዙኃን በመሸጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ መስራትን ይጠይቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመገዳደል፣ በመሰዳደብና በመናናቅ ልናሳካ የምንችለው የፖለቲካ አላማ የከሰረና ወደ ድል የማይወስድ ነው ብለዋል።

እኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብ ዘመኑን ያልዋጀ ውድቅ አካሄድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ አይነት አዝማሚያዎችን በመደገፍ ስልጣን በኃይል ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሥርዓት ለማስያዝ መንግስት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አቋሙን ይደግማል ነው ያሉት።

በመሆኑም መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን በአግግባቡ እንደሚወጣ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህዝቡ እንደ ከዚህ ቀደም የሚያደርገውን ትብብርና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያን ለማበጣበጥና ሰላሟን ለማደፍረስ የሚሰሩ የውጭ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

በደረሰ አማረ