የግብፅ  አፈቀላጤው ዓረብ  ሊግ

በአሳየናቸው ክፍሌ

በግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ተፅፎ የፕሬዝዳንት አል ሲሲ ይሁንታ የሚሰጠው እና በሌላኛው ግብፃዊ የዓረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አህመድ አቡል ገይጥ የሚነበበው የሊጉ መግለጫ በግብፃዊያን ተፅፎ በግብፃዊ የሚነበብ መግለጫ ሲያደርገው በፍርደ-ገምድልነቱ ወደር የለውም፡፡

በምስራቅ ካይሮ በሚገኘው ምስር አል ጄዲዳ ቤተ-መንግስት ተቦክቶ እዛው የሚጋገረው የአረብ ሊግ መግለጫ ሌሎች የሊጉ አባል ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንኳን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ  የሊጉ አቋም በሚል ሽፋን የግብፅን መሻት ብቻ ሲያንፀባርቅ ቆይቷል፡፡

የዓረብ ሊግ ባለፉት 78 ዓመታት በግብፅ መናገሻ ከተማ ካይሮ መሽጎ በሌሎች የአረብ ሀገራት ሽፋንና አጃቢነት የግብፅን ጥቅም ለማስከበር የቆመ ድርጅት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡


በተለይ ግብፅ የህልውናዬ መሰረት ነው ባለችው የአባይ ወንዝ የውሃ ድርሻን ለማስጠበቅ የአረብ ሊግ ለአንድ ወገን ያደላ መግለጫዎችን ሲያወጣ፣ ከ80 በመቶ በላይ ለአባይ ወንዝ ውሃ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን ባይተዋር ባደረገ መልኩ በጉዳዩ ላይ ሲመክር ሲያስፈራራ ሲያስጠነቅቅ ነው የቆየው፡፡

የዓረብ ሊግ ከሰሞኑም ይኸው የተለመደውን የግብፅ መንግስት የፃፈው የሚመስለውን መግለጫውን አውጥቶ ነበር፡፡  የህዳሴው ግድብ ግንባታ አስተዳደር እና የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ባወጣው በዚሁ መግለጫው ሶስቱ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ አጠቃቀሙን በተመለከተ አንድ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው  በማለት ግብፅ ላለፉት ዓመታት የሙጥኝ ያለችበትን አቋም በሊጉ ስም ያንፀባረቀ ሲሆን ኢትዮጵያ የሶስቱ አገራት ትብብር የሌለበት የተናጠል እንቅስቃሴ ልታቆም ይገባል ሲል ሊጉ በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግስትን ተጨባጭ ባልሆነ መረጃ ወንጅሏል፡፡

በአፀፋው በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ መንግስት የዓረብ ሊግ የግብፅ ቃል-አቀባይ በመሆን የህዳሴው ግድብ ግንባታን የፖሎቲካ ጉዳይ ከማድረግ እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡

የህዳሴው ግድብ የአፍሪካዊያነ ጉዳይ እንደመሆኑ ሂደቱ መታየት ያለበት በአፍሪካ መድረክ ብቻ ነው የምትለው ኢትዮጵያ፤ አዲስ አበባን  ባይተዋር በደረገ መልኩ ጉዳዩ የዓረብ ሊግ አጀንዳ እንዲሆን መደረጉ ችግሩን ከማባባስ ያለፈ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም ብላለች፡፡

አሁን ላይ ግብፃዊያን የህዳሴው ግድብ ግንባታም ሆነ የውሃ ሙሌት ማስቆም እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡ እያሉ ያሉት ግን በአባይ ወንዝ ላይ ሌላ ግድብ እንደማትገነቡ ማረጋገጫ ስጡን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አሳሪ ውል ፈርሙልን ነው የሚሉት፡፡

የግብፅ መገለጫ ብዙ ነው፤ በአረብ ሊግ ፍላጎቷን ማስፈፀም ሲያቅታት ወደ አፍሪካ ህብረት ትመጣለች፤ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ዓለም ባንክ ላይ ያለቸውን ተሰሚነት በመጠቀም  ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ብድር እንዳይሰጥ ስታደናቅፍ እና በር ስታዘጋ ኖራለች፡፡ ኢትዮጵያ የማስገንቢያውን ወጭ በልጆቿ ኪስ ተማምና አስጀምራ፣ መሰናክሉን አልፋ፣ የፍጻሜውን ብርሃን በቅርበት እያየች ነው፡፡

የህዳሴው ግድብ አራተኛ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ግብፃዊያኑ ያዙኝ ልቀቁኝ አብዝተዋል፤ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከ ሃዲታ አል-ቃሂራ ጋር በስልክ በደረጉት ቆይታ ጥቅማችንን ለማስከበር ሁሉም አማራጦችን እንጠቀማለን የሚል ድፍረት የተሞላበት ማስፈራሪያ ያዘለ ንግግር አሰምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሞኑ የግብፅ ባለስልጣናት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ እየወጡ ላሉ መግለጫዎች ምላሽ እየሰጠ ሲሆን የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ የሰጡት መግለጫ “ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብሎታል፡፡

በመሆኑም ግብጽ “ድፍረት የተሞላባቸው እና ሕጋዊ ያልሆኑ” መግለጫዎችን ከመስጠት እንድትቆጠብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳስቧል።

ዳግማዊ ዓደዋ የተባለው የህዳሴው ግድብ ከዳር ለመድረስ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን አሁንም ግድቡ ከዳር እስኪደርስ  የጀመረውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት፤ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፡፡