ሀገራቱ በሰራተኛና ፍልሰት አስተዳደር ዙሪያ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተጠቆመ

መጋቢት 8/2015 (ዋልታ) የምስራቅ አፍሪካ አገራት በሰራተኛና ፍልሰት አስተዳደር ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

ህገወጥ ፍልሰትን ለመቀነስ የግሉ ዘርፍ፣ የዳያስፖራውና የአገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 4ኛው የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች የሚኒስትሮች ፎረም የማጠቃለያ መርኃ ግብር ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ወደ ተለያዩ አገራት ከሚፈልሱ ሴቶች መካከል 48 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካውያን መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከምስራቅ አፍሪካ ከሚሰደዱ ዜጎች ውስጥ 50 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ህጻናት እንደሆኑ የዓለም ዐቀፉን የፍልሰት ድርጅት መረጃ ዋቢ በማድረግ ተናግረዋል።

ይህም የምስራቅ አፍሪካ አገራት በሰራተኛና ፍልሰት አስተዳደር ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሚያመላክት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ዐቀፉ የፍልሰት ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር መሀመድ አብዲቀድር ቀጠናው በሚሊዮን የሚቆጠር የሰራተኛ ፍልሰት የሚስተናገድበት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ፍልሰቱን ለመቀነስ የግሉ ዘርፍ፣ የዳያስፖራውና የአገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የማኅበራዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር አይሪን ኢሳቅ (ዶ/ር) በበኩላቸው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የሰው ኃይል ሀገራቱ የስራ እድልን በመፍጠርና ህጋዊ የሥራ ስምሪት ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ከህገ ወጥ ፍልሰት መታደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በጉባኤው በወጣቶች ክህሎትና ስራ ፈጠራ፣ የሀገራት ትብብርን ማጠናከርና የስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ በ5 የተለያዩ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በሙያተኞች ምክክር ተደርጓል።

በሳራ ስዩም