የግጭት አዘጋገብ እና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ለትግራይ ቴሌቪዥን ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው

ግንቦት 03/2013 (ዋልታ) – የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከሰላም ሚንስቴርና ከሌሎች ድጋፍ ሰጭ አካላት ጋር በመተባበር ለትግራይ ቴሌቪዥን ባለሙያዎች የሚሰጠው የድህረ ግጭት አዘጋገብ ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እንድሪስ ጋዜጠኞች በሰላም ግንባታ ላይ ጫናን ተቋቁሞ ለህዝብ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ እንዴት ማተኮር እንደሚቻል እና የመረጃን ትክክለኛነት ማጣራት እንዴት ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ስልጠናው ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የትግራይ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ማህበረሰብ ሬዲዮ ድረስ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን መንገዶች ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንዲመለሱ ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ስልጠናው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ የጋዜጠኝነት መምህራን፣ ሰላም ሚንስቴር ባዘጋጃቸው የግጭት አፈታት ባለሙያዎች እንዲሁም በስነልቦና ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።
(በእንየው ቢሆነኝ)