የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በመመካከርና በመረዳዳት ለሰላም ዘብ እንቆማለን አሉ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በመመካከርና በመረዳዳት ለአካባቢያችን ሰላም ዘብ እንቆማለን ሲሉ ገለጹ፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደርን እና አጎራባች አካባቢዎችን ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ ላይ ያለመ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በዚህም በጎንደር ከተማ አስተዳደር ፋሲል ክፍለ ከተማ እና በላይ አርማጭሆ ወረዳ አስተዳደር በሚገኙ የኩታ ገጠም ቀበሌዎች ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች የአካባቢያቸውን የሰላም እንቅስቃሴ ዘላቂ በማድረግ ረገድ በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

የጎንደርና አካባቢው ሕዝብ ተቻችሎ፣ ተከባብሮና ተሳስቦ ለዘመናት እየኖረ ያለ መሆኑን በመናገር ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ጥቂት ጥቅመኞች የአካባቢውን ሰላም ረፍት ለመንሳት እየሠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የተዋለዱ እና ጠንካራ ማኅበረሰባዊ ውቅር ያላቸውን የቅማንትና የአማራ ሕዝቦች በማጋጨት ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት እንደሆኑም ጠቁመዋል።

አሁንም ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የጎንደርን ሰላም ለማደፍረስና ሀገር ለማተራመስ የሚደረገው ጥረት ሆን ተብሎ የተወጠነ ሴራ መሆኑን ተወያዮቹ ተናግረዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር ተቀባይነት የሌለው እና ሕዝብን የማይወክል መሆኑንም ነው የገለጹት።

እየታዩ ያሉ የሰላም እጦቶች በዋናነት ፖለቲካ ወለድና ሰው ሰራሽ ናቸው ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች በመመካከርና በመረዳዳት ለአካባቢያቸው ሰላም ዘብ እንደሚቆሙ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሔ ለመስጠትም ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግ፣ ለጠላት የማይመች አካባቢ መፍጠር፣ ለግል ጥቅማቸው ብጥብጥን አማራጭ የሚያደርጉ ጥቅመኞችን አሳልፎ በመስጠት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነው ያስታወቁት።