“ኢድ ኤክስፖ” ተከፈተ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) የ”ከኢድ እስከ ኢድ” መርኃ ግብር አካል የሆነው “ኢድ ኤክስፖ” በዛሬው ዕለት ተከፍቷል፡፡

ከኢድ እስከ ኢድ መርኃ ግብር ኢትዮጵያ ያላትን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ማኅበራዊ ሀብቶች በሚገባ ለዓለም የምታስተዋውቅበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የብሔራዊ ጣምራ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናግረዋል።

ከኢድ እስከ ኢድ መርኃ ግብር “የታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” ቀጣይ ምዕራፍ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሯ ዳያስፖራዎች ሀገራቸውን በብዙ መልኩ እንዲያግዙ ያለመ ሀገራዊ ጥሪ መሆኑን አንስተዋል።

ዛሬ የተከፈተው ኤክስፖም የላቀ ምጣኔሃብታዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ዳያስፖራዎች እየጎበኙና እየሸመቱ የኢትዮጵያን ምርት እንዲያስተዋውቁ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሐመድ ኢድሪስ (ዶ/ር) በቀጣይ ቀናት በአዲስ አበባና በክልሎች በሚኖሩ መርኃ ግብሮች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የሀገርና የወገን አለኝታነቱን በተግባር እንዲገልፅ ጥሪ አቅርበዋል።

ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ጣምራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በበኩላቸው ዳያስፖራው በሀገር ቆይታው በወጡ ሁሉም መርኃ ግብሮች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገሩንና ወገኑን የማገዝ ሥራ ላይ በመሳተፍ ወገናዊ አደራውን መወጣት አለበት ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።