የጎንደር ከተማን የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ዓለም አቀፍ አውደርእይ ሊካሄድ ነው

ነሐሴ 1/2014 (ዋልታ) የጎንደር ከተማን የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚያግዝ ዓለም አቀፍ አውደርእይ ሊካሄድ ነው።
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ መላኩ ፋንታ እና አርቲስት ዮሴፍ ገብሬን ጨምሮ ሌሎች አካላት የተሳተፉበት የጥናት ቡድን “Gondar all in one” የሚል ስያሜ የተሰጠው ዓለም አቀፍ አውደርእይ ለማካሔድ የሚያስችል ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።
የአውደርእዩ ዓላማ ከተማዋን የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ያለመ ሲሆን ጎንደር የዓለም ታላቅ ከተማ መሆኗን ማሳየትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል።
የምክረ ሃሳቡን መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የቡድኑ አባልና የፕሮጀክቱ አማካሪ ጋሻው የትዋለ በዕለቱ ለውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለፁት የፕሮጀክቱ ንድፈ ሃሳብ የዓለም አቀፍ፣ ሀገራዊ፣ ክልላዊና የከተማውን የቀደም ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ምክረ ሀሳብ የከተማዋን የባህል፣ የቱሪዝም፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማሳደግ ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ መሆኑንም አንስተዋል።
የአልማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መላኩ ፋንታ በበኩላቸው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ምክረ ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመቀየር በከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች የታየውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።
በፕሮጀክቱ ምክረ ሀሳብ የቅርስ ጥበቃ፣ የዝማሪ ቤቶች፣ የአብነትና የቅኔ ቤቶችን የማሰተዋወቅ ሥራ የፕሮጀክቱ አካል እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
የቡድኑ አባል አርቲስት ዮሴፍ ገብሬ ደግሞ ጎንደር በርካታ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት ነች፤ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ባህል በቱሪዝም ዘርፍ ለገበያ የሚቀርብ ሀብት ነው ብሏል ሲል አሚኮ ዘግቧል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የፓይለት ፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ባህልን ለዓለም ኅብረተሰብ ለማስተዋወቅ፣ የጥምቀት በዓል ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ፕሮጀክቱ በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን ወደ ገንዘብ ለመቀየር ያስችላል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ዘውዱ ማለደ የቀረበው ምክረ ሀሳብ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶችን በመጠቀም የአካባቢውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ምክረ ሃሳቡን ለመተግበር እንሠራለን ብለዋል።