የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ የግል ድርጅቶች የንግድ ፍቃዳቸው እንዳይታደስ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱ ተገለጸ

የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ የግል ድርጅቶች የንግድ ፍቃዳቸው እንዳይታደስ የሚያደርግ የጋራ አሰራር መዘርጋቱን የግል ድርጅቶች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጄንሲው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ክፍያ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን ገልጿል።

አብዛኞቹ የግል ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን የጡረታ መዋጮ በአግባቡ እየከፈሉ ቢሆንም አንዳንዶች ጊዜውን ጠብቀው ያለመክፈል፤ የተወሰኑት ደግሞ የጡረታ መዋጮውን ከነጭራሹ የማይከፍሉበት ሁኔታ መኖሩን ኤጀንሲው አስታውቋል።

የኤጂንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ወዩማ ከጡረታ መዋጮ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ድርጅቶች ላይ የሚስተዋለውን መዘግየትና ለመክፈል አለመፈለግ ችግሮች ለመፍታት በአካል ጭምር በመሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ ደርጅቶች እንዲከፍሉና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ኤጀንሲው ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

በዚሁ መሰረት የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ የግል ድርጅቶች በዓመቱ መጨረሻ የንግድ ፈቃድ እድሳት እንዳይደረግላቸው የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል ነው ያሉት።

ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ክፍያ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የገለጹት አቶ ገመቹ፤ ገቢው በስድስት ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 106 በመቶ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ምክንያት በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳይፈጠር በሚል በተገደበ ጊዜ ውዝፍ ወለድና ቅጣት እንዲነሳ መደረጉ ለዕቅዱ አፈጻጸም ከፍተኛ መሆን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።

“በሌላ በኩል ከሠራተኞቻቸው የጡረታ መዋጮ ቆርጠው ለመንግስት ገቢ የማያደርጉ አንዳንድ ድርጅቶች ለወለድና ለተጨማሪ ቅጣት የሚዳረጉ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

የሠራተኞቻቸው የጡረታ መዋጮ ገቢ ባላደረጉ ድርጅቶች ላይ በተወሰደ እርምጃ ወለድና ቅጣቱን መክፈል ባለመቻላቸው ኪሳራ ውስጥ ገብተው እስከ መዘጋት የደረሱ መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ከግል ድርጅቶች የጡረታ መዋጮ የሚቆረጥላቸው ሠራተኞች ቁጥር 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን መድረሱን ኤጀንሲውን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡