የጤና ስርዓቱን የሚያዘምን የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ለመስጠት ከስምምነት ተደረሰ


ጳጉሜን 1/2015 (አዲስ ዋልታ) የጤና ሚኒስቴር አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችለውን የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ለመስጠት ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ ስርዓቱ ዋና አላማ ፋይዳ የተሰኘውን የዲጂታል መታወቂያ ከጤናው ዘርፍ ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ሰራተኞችና ታካሚዎች ልዩ መታወቂያ እንዲኖራቸው በማድረግ የጤና ምህዳሩ ቀልጣፋ፣ ግልፅ እና የታካሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሰራተኛው እና ታካሚው የተደራጀ መረጃ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባሻገር ሰፊ ሚና የሚጫወት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጤና ዘርፍ አገልግሎት ከዚህ ቀደም በወረቀት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በተለይም የታካሚውን መረጃ ተደራሽ እንዳይሆን ሲያደርግ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡

በሚልኪያስ አዱኛ