ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት የፈፀሙ በማስመሰል ሀሰተኛ ደረሰኝ የሰጡ ሁለት ግለሰቦች በእሰራት ተቀጡ

ኅዳር 22/2015 (ዋልታ) በሀሰተኛ መታወቂያ የወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን በመጠቀም ግብይት ሳይኖር ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት የፈፀሙ በማስመሰል ሀሰተኛ ደረሰኝ የሰጡ ሁለት ግለሰቦች እና በህገወጥ ተግባሩ ላይ የተሳተፈ ግለሰብ በእስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተከሳሽ ተስፋሁነኝ ተሾመ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም በን/ስ/ላ/ክ/ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው ቄራ ዳውን ታውን ህንፃ አካባቢ በሚገኝ ንግድ ቤት ውስጥ በሀሰተኛ መታወቂያ የወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን በመጠቀም ግብይት ሳይኖር 17 ሚሊዮን 940 ሺሕ ብር ሃሰተኛ ደረሰኝ ቆርጦ ሲሰጥ እጅ ከፍንጅ ተይዟል፡፡

በተመሳሳይ ገነት ሀይሉ በልደታ ክ/ከተማ ባልቻ ሆስፒታል አካባቢ ከሚገኝ አሕመድ ህንጻ ውስጥ በሀሰተኛ መታወቂያ በወጣ የግብይት ማሽን ግብይት ሳይኖር 12 ሚሊየን 135 ብር ግብይት እንደተፈፀመ በማስመሰል ሃሰተኛ ደረሰኝ ቆርጣ ስትሰጥ እጅ ከፍንጅ ተይዛለች፡፡

ተከሳሽ ተስፋሁነኝ ተሾመ በፈፀመው ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ በማቅረብ እንዲሁም ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለማዘጋጀትና ለማተም የሚያገለግሉ ማሽኖችን ይዞ በመገኘቱ ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይም ተከሳሽ ገነት ሀይሉ ደግሞ በሀሰተኛ መታወቂያ ስም የወጣ የሂሳብ መመዝገቢያ ማሽን በመጠቀም፣ ግብይት ሳይኖር ሃሰተኛ ደረሰኝ ቆርጣ በመስጠት፣ በተጨማሪም ሕጋዊ ፍቃድ እና ሰነድ ሳይኖራት በሀሰተኛ መታወቂያ ስም የወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ይዛ በመገኘቷ ማሽኑን ተጠቅማ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መግለጫ በማቅረቧ ወይም ደረሰኝ አዘጋጅታ በመስጠቷ ተከሳለች፡፡

ሁለቱም ግለሰቦች በፈፀሙት ተደራራቢ ወንጀሎች እንዲሁም ሦስተኛ ተከሳሽ አብዲ ጃቢር ለራሱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ሃሰተኛ ደረሰኝ እንዲቆረጥ በመደለል ያመቻቸ በመሆኑ ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል፡፡

የሦስቱን ግለሰቦች ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት፤ ተስፋሁነኝ ተሾመ በ 14 ዓመት ጽኑ እስራትና በ360 ሺሕ ብር እንዲሁም ገነት ኃይሉ በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ210 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ሲወስን በአብዲ ጃቢር ላይ የ3 ዓመት ጽኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡