የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ መጀመሩን ገለፀ

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በዛሬው እለት ከሁሉም ክልሎች፣ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር የቪዲዮ ኮንፈረንስ አካሄዷል።

በዚህም 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፣ በቪድዮ ኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው እስከ አሁን በተሰሩ ስራዎች እና ባለው የምርጫ ሂደት ዙሪያ ሐሳብ ሰጥተዋል።

በምርጫ ዝግጅት ዙሪያ በፌዴራል ደረጃ በተዘጋጀ ዕቅድ መሠረት ሁሉም ክልል የራሱን ዕቅድ በማዘጋጀት በየደረጃው ላለው የፀጥታ መዋቅር ግንዛቤ ሰጥቶ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በየክልሉ ባለው የፀጥታ ሁኔታ እና ለምርጫው እንቅፋት ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣ በየደረጃው ያለውን የግንኙነት ስርዓት በማጠናከርና የፀጥታ ስራውን በየ15 ቀን በመገምገም ሁሉም የክልል እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች ከፌዴራል ፖሊስና በየራሳቸውም ቋሚ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልፀዋል።

በጋራ ውይይቱ ላይ የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖችና ሶስት የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በየክልላቸው ያለውን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ በስፋት ማንሳታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።