ከመላ ሀገሪቱ ለተውጣጡ አመራሮች በፌዴራሊዝም መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – የሰላም ሚኒስቴር በፌዴራሊዝም መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ እና አስተምህሮ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና ከመላ ሀገሪቱ ለተውጣጡ አመራሮች እየሰጠ ነው፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ልዩ ድጋፍ ዳይሬክተር ጄነራል ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ እንዳሉት፤ ስልጠናው ከአስሩ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች የሚሰጥ የአሰልጣኞች ስልጠና ነው፡፡

እስከ ታችኛው የማህበረሰብ እርከን ድረስ እንዲወርድ በማድረግ በፌዴራሊዝም መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳብ ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ የስልጠናው ዓላማ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ስልጠናውን የወሰዱ አሰልጣኞች እያንዳንዳቸው 500 የማህበረሰብ አካላትን በየአካባቢያቸው እንደሚያሰለጥኑ እና በአጠቃላይ 452 ሺህ የማህበረሰብ አካላትን በፌደራሊዝም መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ እንደሆነ ፕሮፌሰር ደገፋ ተናግረዋል፡፡

የስልጠናው ዋና ዓላማ በሕገ መንግስቱ በተቀመጠው መልኩ ስለፌዴራል ስርዓቱ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ማህበረሰቡ ስርዓቱን ለማበልፀግ የበኩሉን ሀላፊነት እንዲወጣ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡

ስልጠናው የፌዴራሊዝም ምንነት፤ የፌዴራል ሥርዓት ጥቅሞችና ስጋቶች፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ዋና ዋና ገጽታቻዎች እንዲሁም ፌዴራል ስርዓቱን ለማጠናከር የህዝቡ ሚና በሚሉ ርዕሶች እንደሚሰጥ ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡