የ10 አመታት የልማት እቅድን በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው   

የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ኮሚሽን ባዘጋጀው የ10 አመታት የልማት እቅድን በተመከለተ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

በ10 አመታት የልማት እቅዱ ከተለተያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እየተደረገበት የሚገኝ ሲሆን፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር የሚደረገው የ2 ቀናት ውይይት የውይይቱ አካል ነው ተብሏል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እቅድ ወዳሰብነው ውጤት ሊያደርሰን የሚችል መሳሪያ መሆኑን ገልጸው፣ ከለውጡ በፊት በነበረው ጊዜ ህዝቡን ለማድመጥ ባለመቻላችን በርካታ ችግርች ተከስተዋል ብለዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚመከርበት የልማት እቅዱ ባለድርሻ አካላት በየደረጃው የተሳተፉበት እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ ባለፉት አመታት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ጨምሮ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ የ10 አመቱን እቅድ አስፈላጊነት እንዲሁም ልዩ ባህሪያትን ለተወያዮች አቅርበዋል።

ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ከ2013 እስከ 2022 የበጀት አመታት ድረስ ያለው የ10 አመት የልማት እቅድ ሰነድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ታህሳስ 2 ቀን 2013 መፅደቁ ይታወሳል።

(በቁምነገር አህመድ)