ደቡብ ኮርያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ÷ ኢትዮጵያ ሠላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ስኬት ሀገራቸው አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጹ።

አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ ÷ ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸውና በተለይም ኢትዮጵያ ለኮርያ ልዩ ሀገር መሆኗን አንስተዋል፡፡

አምባሳደሩ ÷ ሠላምና ልማት ለማረጋገጥ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ኢትዮጵያ ኮርያን ጨምሮ ከዓለም ሀገራት ጋር ያላት አጋርነት ለስኬት ያበቃታልም ብለዋል።

ኮርያ በማደግ ላይ ከነበሩ ሀገራት ተርታ ወጥታ ወደ አደጉ ሀገራት ተርታ የተሰለፈች መሆኗን ጠቁመው ይህንን ልምዷን ለኢትዮጵያ እያካፈለች መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡

ኮርያ በኢትዮጵያ የምታካሂደው የልማት ፕሮጀክት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከምታካሂዳቸው መካከል ትልቁ መሆኑንም አንስተዋል።

ሀገራቸው በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርትና በሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ላይ በአጋርነት እየሰራች መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍም፣ በተለይም የሁለቱን ሀገራት የግሉን ዘርፍ ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ 20 የኮርያ ኩባንዎች መኖራቸውንም አምባሳደሩ ጠቁመው በቀጣይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ ቁጥሩ ከፍ እንዲል እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከዚህ ባለፈ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች፤ በአየር ንብረትና በሠላም ማስከበር ላይ ኮርያ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ የምትሰራውን ሥራ ለማጠናከር እንደሚሰሩም  መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አምባሳደሩ በሕዝብ ለተመረጠው አዲሱ የመንግሥት ምሥረታ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።