ዶ/ር ፓትሪክ ሞትስፔ አዲሱ የካፍ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

መጋቢት 03/2013 (ዋልታ) – ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር ዶ/ር ፓትሪክ ሞትስፔ አዲሱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በዛሬው ዕለት 43ኛው የካፍ መደበኛ ስብስባ በሞሮኮ ራባት ከተማ እየተካሄደ ሲሆን የተለየዩ ውሳኔዎችም ተላልፈውበታል፡፡
ከእነዚህ መካከል በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተከናወነ ሲሆን ተመራጭ ሆነዋል፡፡

በካፍ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከደቡብ አፍሪካዊው ቢሊየነር በተጨማሪ በእጩነት የቀረቡት ሌሎች ሶስት ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉ ሲሆን ያለምንም ቅሬታ በሙሉ ድምፅ ነው የተመረጡት፡፡

በዛሬው ጉባኤ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂኒ ኢንፋቲኖን ጨምሮ የካፍ አባል ሀገራት ተገኝተዋል፡፡

ተመራጩ ዶ/ር ፓትሪክ ሞትስፔ በደቡብ አፍሪካ ሊግ የሚወዳደረውን ማሚሎደሰንዳውን ላለፉት ሁለት አመታት በፕሬዝዳንትነት መምራታቸውም ተገልጿል፡፡

በዚህ ሹመት ደግሞ በቅርቡ ከሙስና እና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ከስልጣናቸው የተሰናበቱትን ማዳጋስካራዊውን አህመድ አህመድን ተክተው ለቀጣይ አራት አመታት የአፍሪካን እግር ኳስ በበላነት ይመራሉ፡፡
(በሐብታሙ ገደቤ)