ጣሊያን የወረርሽኙ ሥርጭት በመጨመሩ ሱቆችንና ትምህርት ቤቶችን ልትዘጋ ነው

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንደተከሰተ ከሌሎች አገራት ቀድማ በርካታ ዜጎቿን ባጣችው ጣሊያን፤ አሁንም የቫይረሱ ሥርጭት አለመገታቱ ተገለጸ።

በዚህም ምክንያት ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች በበርካታ የአገሪቷ ክፍሎች ከሰኞ ጀምሮ እንደሚዘጉ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪዮ ድራጊ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደሚያጋጥምም አስጠንቅቀዋል።

በፋሲካ በዓል አካባቢ ባሉት ሦስት ቀናትም ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ይጣላል ተብሏል።

በአዲሱ የእንቅስቃሴ ገደብ ሕዝብ የሚበዛባቸውን ሮምና ሚላንን ጨምሮ በግማሹ የጣሊያን ክፍል ትምህርት ቤቶች፣ ሱቆችና እና ምግብ ቤቶች ከሰኞ ጀምሮ ዝግ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ከሥራ፣ ጤና ወይም ከሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ከሌላቸው በስተቀር ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ይገደዳሉም ተብሏል።

እነዚህ ገደቦች እስከ ፋሲካ ድረስ እንደሚቆዩም የጠቅላይ ሚኒስተር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ይህ መሆኑ በልጆች ትምህርት እና ኢኮኖሚ ላይ ተፅእኖ የሚያደርግ ቢሆንም ሥርጭቱን ለመግታት ግን ግድ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጣሊያን የመጀመሪያውን የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እየታገለች መሆኗ ተገልጿል።

እስካሁን አገሪቷ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን በሞት አጥታለች። በዚህም በአውሮፓ ካሉ አገራት ከዩናይትድ ኪንግደም ቀጥላ ከፍተኛ ሞት የተመዘገበባት አገር ሆናለች።

በጣሊያን ባለፈው ዓመት ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ 3.2 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ይሁን እንጅ በሌሎች የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት እንደታየው በጣሊያንም የክትባት ዘመቻዎች መዘግየት አጋጥሞታል።

ባለፈው ሳምንት የጣሊያን መንግሥት የክትባት እጥረትን ለመቀነስ 250 ሺህ ብልቃጥ የኦክስፎርዱን አስትራዜኔካ ክትባት ወደ አውስትራሊያ እንዳይላክ አግዶ ነበር።

በሌላ በኩል በቡልጋሪያ፣ ዴንማርክ እና ኖርዌይ የኦክስፎርዱን አስትራዜኔካ ክትባት የደም መርጋት ያስከትላል በሚል ስጋት መጠቀም አቁመዋል።

ይሁን እንጅ የዓለም ጤና ድርጅት አርብ ዕለት ይህ እውነት መሆኑን የሚያረጋገጥ ማስረጃ እንደሌለ አስታውቆ አገራቱ ክትባቱን መጠቀም ማቆም እንደሌለባቸውም በአፅንኦት አሳስቧል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።