በመተከል ዞን አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም የማስፈን ስራው ተጠናከሮ ይቀጥላል

መጋቢት 03/2013 (ዋልታ) – በመተከል ዞን አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እየተሰራ ያለው ሰራ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል የተቀናጀ ግብረ ሃይሉ አስታውቋል።
በመተከል ዞን ሠላም ለማስፈን የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል በሁለት ወራት በተከናወኑ ተግበራት ላይ ለሁለት ቀናት ከተወያየ በኋላ ለቀጣይ ስራ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በዞኑ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ መደፍረስ ለማረጋጋት በተቋቋመው ግብረ ሃይል በፀጥታ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ መስኮች የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸው ተገልጿል።
የግብረ ሃይሉ መሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ባለፉት ሁለት ወራት የአገር መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በዞኑ አንፃራዊ ሠላም ተረጋግጧል ብለዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጎን ለጎን ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በተሰራ የሠላም ጥሪ ከ3 ሺህ በላይ ታጣቂ ሃይሎች በሠላማዊ መንገድ እጅ መስጠታቸውንም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻም ታጣቂው ሃይል ሲንቀሳቀስባቸው የነበሩ ከ170 በላይ ቀበሌዎችን ነፃ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።