መጋቢት 29/2015 (ዋልታ) የጋቦን ፓርላማ የአገሪቱን ፕሬዝዳንት የስልጣን ዘመን ቆይታ ከሰባት ወደ አምስት ዓመት ዝቅ እንዲል ውሳኔ አሳለፈ፡፡
ውሳኔው የተላለፈው አገሪቱ ቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከአምስት ወራት በኋላ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት መሆኑን ፍራንስ ቲዊንቲ ፎር አስነብቧል፡፡
በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱን ለመምረጥ በሁለት ዙር ይደረግ የነበረው ምርጫ በአንድ ዙር እንዲካሄድም ተወስኗል፡፡
ውሳኔው ብሔራዊ ሸንጎው እና ሴኔቱ በዋና ከተማዋ ሊበርቪል ተሰብስበው የቀረበውን የማሻሻያ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ ከደገፉት በኋላ መሆኑም ተነግሯል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደገለጹት ስምምነት ላይ የተደረሰው በገዥው እና ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጋር ለአስር ቀናት ከተደረገ ፖለቲካዊ ምክክር በኋላ ነው፡፡
በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2009 ከአባታቸው ኦማር ቦንጎ ኦንዴምባ ስልጣን የተረከቡት ያሁኑ ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ጋቦንን ለ41 ዓመታት የመሩ ሲሆን አሁንም በእጩነት እንደሚቀርቡ በሰፊው ይጠበቃል፡፡
በነዳጅ ሃብቷ የናጠጠቸው ጋቦን በቦንጎ ቤተሰብ አገዛዝ እና በጋቦን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲያቸው ስር መተዳደር ከጀመረች ከ55 ዓመታት በላይ መመራቷን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡