ሚያዝያ 21/2013 (ዋልታ) – ግብጽና ሱዳን የጀመሩት አዲስ ስትራቴጂ በኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች እንዲፈጠሩና እንዲባባሱ በማድርግ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ጥረት ማድረግ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
በኢትዮጵያ ያለውን የብሄር ፖለቲካ አደረጃጀት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ አገሮቹ ዓላማቸውን ለማሳካት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባይ ተፋሰስ አገራት 11 ቢሆኑም ግብጽና ሱዳን ግን የቀኝ ግዛት ውሎችን በመጠቀም ለዘመናት በብቸኝነት ሲጠቀሙ የቆዩ ሲሆን አሁንም በዚሁ የመቀጠል ፍላጎታቸውን ይዘው እየሰሩ መሆኑንም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
በተለይም ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት እንዳትጠቀም ለዘመናት በመሰራቱ በርካታ ዜጎቿ በድህነት አረንቋ ውስጥ ህይወታቸውን እንዲያሳልፉ ተገደዋል።
ለዚህ ደግሞ የውስጥና የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫናዎች እንደ አይነተኛ ምክንያት ሆነው የሚወሰዱ መሆኑን ምሁራኑ ይናገራሉ።
የግድቡ ግንባታ እንዲስተጓጎል በውስጥና በውጭ የሚሰሩትን መሰናክሎች በማለፍ ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት እውን ለማድረግ መዘጋጀቷ ግብፅና ሱዳን ይሳካል ብለው ያልጠበቁት ስለሆነ ለማስተጓጎል የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ምሁራኑ ያብራራሉ።
በኢትዮጵያ ስራ አመራር አካዳሚ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ እንደሚሉት ሁለቱ አገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዳይኖር በመጣር የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል እየሰሩ ነው።
የታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ እንደሚሉትም ግብፅና ሱዳት በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር አቅደውና ተዘጋጅተው እየሰሩ ይገኛሉ።
አገሮቹ የውስጥ ልዩነቶችን በማስፋት የኢትዮጵያን ልማት የማስተጓጎል ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ ያለው ብሄር ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ምሁራኑ ያምናሉ።
በመሆኑም የአገሮቹን አደገኛ አካሄድ መንግስትም ሆነ እያንዳንዱ ዜጋ ተረድቶ የውስጥ ልዩነቶችን በማጥበብና በንግግር በመፍታት ለአገር ሉዓላዊነት እና ለህዝቦች ደህንነት በጋራ መቆም ይገባል ብለዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን አገሮች የሚያከናውኗቸውን የልማት ስራዎች በእውቀትና በትብብር መሆኑን ገልጸው ይሁንና ግብጽ የያዘችው የብቸኛ ተጠቃሚነት አቋም በማንም ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
ሶስቱ አገሮች ድንበር ተሻጋሪውን የናይል ወንዝ በትብብርና በፍትሃዊነት ለመጠቀም የማንም ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልጋቸው ስምምነት ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል።
ሆኖም ግብጽና ሱዳን ጉዳዩን አለም አቀፋዊ በማድረግ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ መጠቀም የለባትም በሚል የሚያራምዱት ጭፍን አስተሳሰብ እየከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኢዜአ የተገኘው መረጃ እንዳመላከተው የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊያን በአግባቡ መፍትሄ ማግኘት ስለሚችሉ የሶስትዮሽ ድርድሩ በቀጣይም በአፍሪካ ህብረት ሊካሄድ ይገባዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የውሃ ሀብት አኳያ እየተጠቀመች ያለው 25 በመቶ ብቻ መሆኑን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ ከ65 በመቶ በላይ ዜጎቿ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ካለመሆናቸውም በላይ ኢንዱስትሪ እንዳይስፋፋ እንቅፋት ሆኗል፤ ይህ ደግሞ የድህነት መንስኤና ዜጎች የስራ እድል አንዳይፈጠርላቸው ማነቆ ሆኗል።