ግብጽ በ2 ወራት ብቻ 57 ሰዎችን በስቅላት ቀጣች

ግብጽ በሞት የምትቀጣቸው ፍርደኞች ብዛት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ።

ግብጽ ባለፉት ጥቅምትና ኅዳር ወራት ብቻ 57 ሰዎችን በስቅላት እንደቀጣችና ይህም በፈረንጆች 2019 በስቅላት ከተቀጡ ጠቅላላ ሰዎች እጥፍ በ2 ወራት ብቻ መፈጸሙን እንደሚያሳይ ተጠቁሟል፡፡ ግብጽ በአምነስቲ ዘገባ ላይ ያለችው ነገር የለም።

ባለፈው ወር አምነስቲ ባወጣው አንድ ሪፖርት በግብጽ የሰብአዊ መብት አያያዝ ማሽቆልቆል ላይ የሰላ ትችት ሰንዝሮ ነበር።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ እንደሚለው በቁጥር በርከት ያሉ ተቃዋሚዎች እና የመብት ተቆርቋሪዎች በግብጽ ብዙ ውጣ ውረድ እየደረሰባቸው ነው።

ግማሾቹ የታሰሩ ሲሆን ቀሪዎች ደግሞ ከአገር እንዳይወጡ መደረጉንና አንዳንዶቹ ደግሞ በአልሲሲ መንግሥት ሀብትና ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ ተወስኖባቸዋል።

አልሲሲ በ2013 ወደ ሥልጣን የመጡት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን ላይ የወጡትን ሟቹን መሐመድ ሞርሲን በመፈንቅለ መንግሥት ከጣሉ በኋላ ነው።

በአብላጭ ድምጽ ወደ ሥልጣን መጥተው የነበሩት ሙሐመድ ሙርሲ በእስር ቤት ሳሉ ታመው ብዙም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ መሞታቸው ይታወሳል።

አልሲሲ በአገሬ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም የሚሉ ሲሆን፣ የአምነስቲ መረጃ እንደሚያስረዳው በግብጽ በስቅላት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር በአንድ ጊዜ ማሻቀብ የጀመረው በካይሮ እጅግ ጥብቅ እንደሆነ ከሚነገርለት ከቶራ እስር ቤት ፍርድኞች ለማምለጥ ከሞከሩ ወዲህ ነው።

በእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረው በርካታ የሞት ፍርደኞችና ፖሊሶች መሞታቸው አይዘነጋም።

ግብጽ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሰብአዊ መብት ድርጅቶች የሚሰሩ በርከት ያሉ ዜጎቿን በማሰሯ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ከመብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍ ያለ ወቀሳ ሲቀርብባት ከርሟል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ሕግን የማስከበር እርምጃ ተወሰደ እንጂ ሌላ የሆነ ነገር የለም ይላሉ።