ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – ግብፅ የውሃ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የህዳሴ ግድቡን እንደ መሳሪያ በመጠቀም ኢትዮጵያን አሳሪ ስምምነት ለማስፈረም እየሰራች ነው ሲሉ አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እና የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ም/ቤት ፅ/ቤት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
በዚሁ መድረክ ላይ ያለፉ የድርድር ሂደቶችንና የግድቡ ግንባት ሂደት ላይ ጽሑፎች ቀርበዋል።
በቀረበው ጽሑፍም ግብፅ የውሃ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የህዳሴ ግድቡን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመችበት መሆኑ ተመላክቷል።
ይህንን ጥቅሟን ለማስጠበቅም ኢትዮጵያ ለድርድር ፈቃደኛ አይደለችም የሚል ሀሰተኛ አካሄድን በመከተል የ3ኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንዲኖር በማድረግ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ በመክተት አሳሪ ስምምነት ውስጥ ለመክተት እየሰራች መሆኑም ተብራርቷል።
ኢትዮጵያ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚል አቋምን እንደያዘች የቀጠለች ቢሆንም ግብፅ እና ሱዳን ግን ህልውናችን አደጋ ላይ ነው በሚል የዓለም አቀፍ ትኩረትን በማግኘት የተቻኮለ ዓለም አቀፍ ስምምነት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያን ማሰር ዋነኛ ዓላማቸው ነውም ተብሏል።
ኢንጅነር ጌዲዮን አሰፋ እንደገለፁት እያንዳንዱ ግብፃዊ በዓመት በሰዓት 1800 kw የሀይል ፍጆታ ሲኖረው 86 በመቶ ያህል የውሃ አስተጥፅኦ ባላት ኢትዮጵያ የአንድ ግለሰብ የሀይል ፍጆታ 73 kw መሆኑ ታውቋል፡፡
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ የምታምን ሲሆን ድርድሩም በውሃ ሙሌት ዙሪያ እንጂ ተጠቃሚነቷ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል።
(በትዕግስት ዘላለም)