ግጭቶችን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን ማበጀት ይገባል ተባለ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) በምሥራቅ አፍሪካ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን ማበጀት እንደሚገባ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ስትራቴጂክ ከፍተኛ የአማካሪዎች መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በምሥራቅ አፍሪካ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመከላከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን ማበጀት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ስትራቴጂክ ከፍተኛ የአማካሪዎች ሚና ከፍተኛ መሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የአማካሪዎቹን ቡድን እንደ ተቋም ማደራጀት ለሰላም ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሩ አፍሪካዊያን ያሉንን በጎ እሴቶችና ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም ለሰላም መረጋገጥ ማዋል ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል ጌታቸው ሽፈራው በቀጣናው የሚታዩ የፀጥታ ችግሮችን ለመከላከል የተለያዩ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣናው ግጭቶች ሳይፈጠሩ ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ስልት ተነድፎ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ዶሚቲን ንዳይዜ ጨምሮ ከአስሩ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የቀድሞ አምባሳደሮችና ከፍተኛ የጦር አመራሮች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡